Sunday, September 23, 2012

“መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ…”



ጎልጉል ፦ የጠ/ሚኒስትር መለስ መታመም ድንገተኛ ነው የሚሉ አሉ፤ አሟሟታቸውም ድንገት ነው የሚሉ አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አጋጣሚው መልካም እንደሆነ የሚጠቁሙ አሉ አንተ ከየትኛው ወገን ነህ?
መልስ፦ ቅድሚያ አቶ መለስ ድንገት አልታመሙም። በሽታቸው የቆየ እንደሆነ ይታወቃል። ምስጢርም አይደለም። ለዚሁ እኮ ነው ቤተ መንግስት ውስጥ በአዋጅ የተፈቀደላቸውን ቤት አሰርተው በቅርብ ርቀት እየተቆጣጠሩ ለመኖር ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ የነበረው። በዚህ ቢስተካከል ለማለት ነው። መለስ ለኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ሁሉ የጋራ ነጠብ ናቸው። በድልድይም ይመሰላሉ። በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፣ በተለይም ዋናዎቹ አራት ፓርቲዎች በውስጣቸው የያዙት 21 ዓመትና ከዚያም በላይ የታመቀ ቁርሾ አለ። የመለስ ማለፍ በየድርጅቱ ታፍኖ የኖረውን ቁርሾ ማፈንዳቱ አይቀርም። ከዚህ አንጻር ሳየው የመለስ ሞት አጋጣሚው መልካም የሚሆንበት አግባብ ከምን እንደሆነ ልረዳው አልችልም።
ጎልጉል አዲስ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል አጋጣሚ ይሆናል ነው የሚሉት፤
መልስ፦ ምን አይነት አዲስ ስርዓት? አሁን እኮ ሁሉም ነገር “ባለበት፣ በነበረበት፣ በቀድሞው መልክ ይቀጥላል” እየተባለ ነው። እነሱም ባይናገሩ ህወሃት ወደ እርቅና ድርድር የመመለስ ፍላጎት ይኖረዋል ብዬ ለሰኮንድ አላስብም። ህወሃቶች አንገት ለአንገት ተናንቀው ትግል የሚያደርጉት ተቃዋሚ ከሌለ ብቻ ነው። ለህወሃት መኖር ፈተና የሚሆን ተቃዋሚ ካለ ህወሃቶችም ሆኑ በትግራይ ውስጥ መሰረት ያላቸው ተቃዋሚዎች ልዩነት አያሳዩም። ይህ ሳይታበል የተፈታ እውነት ነው። በ1997 ምርጫ ወቅት የታሰሩት የቅንጅት አመራሮች ሲፈቱ ደስተኛ አልነበሩም። እንዴት እንደተፈቱና ሂደቱ በህወሃት ውስጥ የፈጠረው ውዝግብ የሚረሳ አይመስለኝም። ሌላው ቀርቶ በወቅቱ የምርጫውን ውጤት ቅንጅት ማሸነፉ ሲታወቅ ህወሃት ያገለላቸው እንኳን ሳይቀሩ አንድ ላይ በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ተማምለው ነበር። ታጥቀውም ነበር። ከዚህም በላይ…
ጎልጉልግምት አይመስልም? ምን ማስረጃ አለ? ኢትዮጵያዊ የሆኑና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ተቀላቅለው የሚሰሩ ….
መልስ፦ ላቋርጥህ፤ ኢትዮጵያዊ ቀለም የተቀቡ የህወሃት የቀድሞ ባለስልጣኖች በህወሃት ህልውና ላይ የሚፈረድበት የመጨረሻ ቀን ቢመጣ የመጀመሪያዎቹ ተቃዋሚዎች እነሱ እንደሚሆኑ እምነቴ ነው። መቃወም ብቻ አይደለም ህወሃትን ወዲያው ተቀላቅለው የህወሃትን ባንዲራ እንደሚለብሱ አልጠራጠርም። እነዚህ ሰዎች የወደፊቱ አደጋ የታያቸው ናቸው። ህወሃት ሳይቀበር፣ ኃይሉም ሳይመናመን እርቅ እንዲወርድ ግን ይፈልጋሉ። ልክ እንደ አቶ መለስ እነሱም ለክፉ ቀን ድልድይ ለመሆን ራሳቸውን ያዘጋጁ ናቸው፤
ጎልጉልአይታመኑም እያልክ ነው?
መልስ፦ ከህወሃት ባህሪ አንጻር ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ ማየት አይከፋም። የተቃዋሚ ፓርቲዎች የጓዳቸውን ቁልፍ እያባዙ ማንንም ሳይመርጡ ይሰጣሉ። ለማን ሰጥተው ለማን እንደሚከለክሉ አልተረዱም። ህወሃት ውስጥ ሆነው ሙሉ መረጃ የማያገኙ አጫፋሪዎች አሉ። እዚህ ደግሞ ተቃራኒ ነው። ህወሃት ለወለዳቸው አገልጋዮቹ መረጃ ይደብቃል። ተቃዋሚዎች ግን ምስጢር መደበቁ ቀርቶ በራቸውን እንኳ ገርበብ አያደርጉም።
ጎልጉልበመጠራጠር ብቻ ማግለል ትግሉን ሲጎዳ የኖረ አብይ የትግል ስህተት እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፤
መልስ፦ እንግዲህ ይህ የኔ አስተያየት ነው። ይህንን አስተያየት ስሰጥ ተቃውሞ ሊነሳ እንደሚችል አውቃለሁ። ቅር የሚሰኙ ክፍሎችም ይኖራሉ። የ97 ምርጫ ብዙ ትምህርት የሰጠን ይመስለኛል። በፖለቲካ ቁርጠኝነት ማነስና አርቆ ማሰብ ባለመቻሉ አጋጣሚው፣ ያ አሳዛኝ የህዝብ ተነሳሽነት፣ አገሪቱን ሙሉ ያነቃነቀው የለውጥ ማዕበል መጨረሻው አንገት የሚያስደፋ ሆኗል። ከዛ ግን አሁን ድረስ መማር አልቻሉም። በወቅቱ ፍርሀት ነግሶባቸው የነበሩት ክፍሎች ያለ ልዩነት ተደራጅተው መመሪያ ይጠብቁ ነበር። ሌላው ወገን ደግሞ ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራትና ያዘዘው ሰላማዊ ተቃውሞ እንዳይደረግ እየፈራ አቋም ይቀይር ነበር። ፖለቲካኛ መሆንና አገር ወዳድ መሆን አንዳንዴ ይለያያሉ። አንድ ግምገማ ላይ እነዚህኑ ሰዎች ጥሩ አባቶች እንጂ ፖለቲከኞች አይደሉም ብለው ተርተውባቸዋል። እውነት ነው። መንግስት የሚፈራው ልደቱን ነበር። ልደቱ የገባው ፖለቲከኛ ነው። የዛሬን አያድርገው ማለቴ ነው።
ጎልጉልምን ለማድረግ ነበር የተደራጁት?
መልስ፦ ሌላ ጥያቄ የለህም?

ጎልጉልወደ ድልድዩ ምሳሌ እንመለስ፤
መልስ፦ አቶ መለስ ብቃት አላቸው በሚል በሁሉም የኢህአዴግ ፓርቲዎች ይታመናል። ስለዚህ ለሁሉም ፓርቲዎች እሳቸው የጋራ ነጥብ ናቸው። ድልድይ ናቸው። እሳቸው አመራር ላይ ከሌሉ ይህ ድልድይ ተሰበረ ማለት ነው። ድልድዩ ከተሰበረ ግንኙነት የለም ማለት ነው፡፡ኢህአዴግ የጋራ ነጠብ ከሌለው ምን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ ብዙ ምርምር አያስፈልግም።
ጎልጉልእስከዛሬ እኮ አብረው እየሰሩ ነው፤ ድርጅት አለ፤ መዋቅር አለ፤ ችግር የለም እያሉ ነው፤
መልስ፦ ህወሃት ከኦህዴድ ወይም ከብአዴን ወይም ከደህዴን ጋር ፊት ለፊት ተወያይቶ ወይም ባንድ ጉዳይ ላይ በጋራ ተሟግቶ አያውቅም። መለስ ናቸው መሃል ላይ ሆነው የሚያገናኙዋቸው። ግንኙነቱም የተገነባው ለመለስ ስብዕና አምኖ በመገዛትና ትዕዛዝ በመቀበል እንጂ በሌላ መልኩ አይደለም። ይህ መለስ ላይ የተቸከለ ግንኙነት በእኩል ተሰሚነትና ፖለቲካዊ ሚና ላይ ያተኮረ ስላልነበር ጤነኛ አይደለም። በዚህ መነሻ አባል ድርጅቶቹ የሎሌነት ተግባር ሲያከናውኑ ኖረዋል። ይህንን እውነት ሁሉም ወገኖች ያውቁታል። አቶ መለስም በደንብ ጠንቅቀው ያውቁታል። የድራማው ተዋናይ እሳቸው ስለሆኑ በልዩነት ውስጥ የጋራ ነጥብ ሆነው ሁሉም “መለስ ከሌለ ህወሃት/ኢህአዴግ ባዶ ነው” እያሉ 21 ዓመታት ዘልቀዋል። ህወሃቶች በአጋር ፓርቲዎች እንደማይወደዱ ስለሚያውቁ ሁሌም ዝግጁ ናቸው። ሌላው ትልቁ ነጥብ ደግሞ በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ያሉት ሎሌዎች ሰው መሆናቸውና ትልቁ ፍርድ ቤት የሚባለው ህሊናቸው ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በግል “ተታለሃል፣ እስከመቼ መጫወቻ ትሆናለህ” እያለ ሲሞግታቸው ነው የኖረው። ለዚህ ነው የመለስ ከስልጣን መለየት የሚያመጣው ጣጣ ቀላል የማይሆነው። አማራው ላይ የተፈጸመው፣ ኦሮሞዎች ላይ የተካሄደውና የህወሃት ሰዎች “ለመግዛት የተፈጠርን ነን” በሚል የሚያሳዩዋቸው ንቀት ቀን የሚጠብቅ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ …
ጎልጉልበአሁኑ ሰዓት እኮ “ሰው ቢሄድ ስርአትና ተቋም ባለበት ይቀጥላል” የሚል አቋም እየተንጸባረቀ ነው ያለው፤
መልስ፦ አቶ ስብሃት (the kingmaker) ለአሜሪካ ሬዲዮ ይህንን ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ጥያቄው ኢትዮጵያ ውስጥ ተቋም አለ ወይ የሚለው ነው። ተቋም የለም። ሁሉም ነገር አቶ መለስን ማዕከል ያደረገ ነው። መለስ መሞታቸው ይፋ ከሆነበት ቀን ጀምሮ የምንሰማው ምስክርነት ስለ መለስ ብቻ ነው። ባለስልጣኖችና አንጋፋ የፖለቲካው ፊታውራሪዎች ፋይዳ እንዳልነበራቸው ባደባባይ በተደጋጋሚ ባንደበታቸው እየተናገሩ ነው። ወደፊትም ይናገራሉ። አያያዛቸው የሚያቆም አይመስልም። ስለዚህ የኔ አስተያየት አያስፈልግም። የኢህአዴግ የፕሮፖጋንዳ ሰለባ የሆነው ህዝብና የበታች ካድሬ ለቅሶ ደራሽና ደረት ደቂ የሆኑት ወደው ሳይሆን በመለስ ስብእና ላይ የተመሰረተው ቅስቀሳና ትምህርት ሰለባ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ለኔ ይህ ትልቅ አደጋ ነው። በብዙ መልኩ አደጋ አለ የሚባለውም ለዚህ ነው። ተቋም ቢኖር ኖሮ ምንም ስጋት የለም። ሁሉም ነገር ስርዓቱን ጠብቆ ይሄዳል። የአቶ መለስ መሞትም ስጋት ባልሆነም ነበር። ሌላው ትልቁ ስጋት አገሪቱ ውስጥ የተቋቋሙ፣ ህዝብ ላይ ንግድ ቤት የከፈቱ የስርዓቱ ውጤቶች ናቸው።…
ጎልጉልእንዴት?
መልስ፦ ባለኝ መረጃ መሰረት የኔ ስጋት እነዚህ ያለቀረጥ የሚነግዱ፣ ገንዘብ የሚያቀባብሉ፣ የገንዘብ ዝውውር ላይ የተሰማሩ፣ ድርጅት ያላቸው፣ በቅጽበት ተመንጥቀው ባለሚሊዮኖች የሆኑ፣ የባንክ ብቸኛ ተጠቃሚዎች፣ ሸቃጮችና አወራራጆች ከትንሽ እስከትልቅ ስራውን የሚሰሩት ከባለስልጣናት ጋር ነው። ከመከላከያ አመራሮች ጋር ነው። ከደህንነትና ከዋናው የስልጣን እርከን ጋር በመመሳጠር ነው። እነዚህ ሁሉ የራሳቸው ትናንሽና ተንቀሳቃሽ መንግስታት አላቸው። አቶ መለስ በህይወት እያሉ ይህንን ጠንቅቀው ያውቁታል። ግን ልንካው ቢሉ ህይወታቸው አደጋ ውስጥ ይወድቃል። “ገምተናል” ሲሉ አስቀድመው የተናገሩት ይህንኑ ነው። እና ተቋም የለም። አቶ ስብሃትና አብረዋቸው ያሉ በትምክህት የሚያስቡት ከአሁን በኋላ ያለችውን ኢትዮጵያን ለመግዛት የተፈጠሩ፤ አቅሙና ችሎታው ያላቸው እነሱ ብቻ እንደሆኑ ነው። ግን አውነታው እነሱም ድርጅታቸውም ፍልስፍናቸውም መበስበሱ ነው። የመበስበሳቸው ምልክቶች ሞልተው ፈሰዋል። ሁሉም በዝርፊያ ባህር ውስጥ እየዋኙ ነው። የሚገርመው እንደዚህ በስብሰው አገርና ህዝብ ለመምራት በየቀኑ መገዘታቸው ነው፤
ጎልጉልባለሃብቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ እድል ፈንታ ላይ አሉታዊ ሚና አላቸው እያልክ ነው?
መልስ፦ ምን ጥርጥር አለው። ስርዓት ሲበሰብስ ልዩ ምልክቱ ትናንሽ መንግስታት ማቆጥቆጣቸው ነው። በኢህአዴግ መበስበስ አቶ መለስን ጨምሮ በርካቶች ይስማማሉ። ኢህአዴግ መዓዛውን አልቀየረም የሚሉት በአገሪቱ ድፍን ቆዳ ላይ የራሳቸውን መንግስት የተከሉ ተጠቃሚዎች ብቻ ናቸው። እነሱ ክሬሙን እየላሱ ስለሆነ የመበስበስ አደጋ አይታያቸውም። ስለመበስበስ ለማሰብም ጊዜ የላቸውም። የበሰበሰው ነገር ሲናድ የሚበላው ግን አስቀድሞ እነሱን ነው። ምክንያቱም አቶ መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ በጣም ትልቅ ነው። እስካሁን የገባበት የለም። አፉን ከፍቶ የሚጠብቀው። ጉድጓዱ የሚውጠውን አሰፍስፎ እየጠበቀ ነው። በስብሶ ማበስበስ የመለስ ፍልስፍና ውጤቱ አፉን የከፈተውን ትልቅ ጉድጓድ መሙላት ነው። በነገራችን ላይ እነዚህ ሃብታሞች ናቸው ስርዓቱን በስለላና የተቃዋሚ ወዳጆችን በማባበል መረጃ በማሰባሰብ የሚያገለግሉት። የኪነት ሰዎችን በኮንሰርትና በበዓላት እያሳበቡ ኢህአዴግ ጉያ ውስጥ በመክተት ህዝብ የሚወዳቸውን ሰዎችና ባለሙያዎች የሚያዋርዱት። ታዋቂ ሰዎችና የሚወደዱ ባለሙያዎች የበሰበሰውን ሰፈር ሲቀላቀሉ ህዝብ ተስፋ ይቆርጣል። ሌላም ብዙ ስራ አላቸው።
ጎልጉልስለዚህ የተለየ ምንም አጋጣሚ የለም እያልክ ነው?
መልስ፦ እውነቱን መነጋገር የሚበጅ ይመስለኛል። በመጀመሪያ ደረጃ ህወሃት አናሳ ቁጥር ያላቸውን ይዞ፣ ከዚያም ወርዶ በጎጥና በቀበሌ ደረጃ የሚርመጠመጥ ድርጅት ነው። ሰፊ ቁጥር ያላቸውን ሁሉ በሃይል እየገዛ ያለው በነጻ አውጪ ስም ተሰይሞ መሆኑ ደግሞ ይገርማል። መንግስትም ሆኖ ነጻ አውጪ ነው። ነጻ አውጪ የት አገር ነው መንግስት የሚሆነው። ራሱ መንግስት ከሆነ ከማን ነው ነጻ የሚወጣው? የሚጨቆኑና ነጻ የሚሆኑ ዜጎች እንዳሉ በማስመሰል ህገመንግስታዊ ዋስትና ይዞ የሚጠባበቀው ለምንድነው? ከአንቀጽ 39 ጋር ቅበሩኝ የሚለው ለምንድነው? የፖለቲካው መክረርና የፖለቲካው ጨዋታ ዞሮ ዞሮ እዚህ ነጥብ ላይ ነው። በፍርሃትና በዚህ መልኩ መቀጠል ስለማይቻል “እነሱ ከሌሉ አገር ይፈርሳል” እያልን እንድንገዛ የተቀመጠልን ቀልድ ነው። ከትግራይ በላይ በርካታ አማራጭ ያላት ኤርትራ እንኳ የገባችበትን ጣጣ እያዩ … ለሁሉም መድሃኒቱ የተለየና ለአገራችንና ለሁሉም ወገኖች የሚበጅ የሰላምና የጨዋ ፖለቲከኞች ስምምነት ወሳኝ ነው። እንደ አማራጭ የሚቀርበው ታላቅ ጉዳይም እርቅና እርቅ ነው። ግን ህወሃት እርቅ ይቀበላል? አይመስለኝም። ከድርድር በኋላ ምን እንደሚከተል እኮ ያውቃሉ። እርቅ ሲፈጠር ተቋማት ይፈርሱና እንደገና ይዋቀራሉ። የግል ፋይል ይበረበራል። ነጻ ፍርድ ቤቶች ይቋቋማሉ። ጳጳሱ፣ ካድሬው፣ የፖለቲካው አስፈጻሚዎች፣ ኢህአዴግ ያፈራቸው ባለሃብቶች፣ ተጠቃሚዎች… አድርጉ የተባልነውን ስናደርግ ኖረን እንዴት እርቅ ትላላችሁ በሚል ተቃውሞ ያሰማሉ። አቶ መለስ እንዳሉትና እኔም እንደማምንበት ድርጅቱ ስለበሰበሰ የበሰበሰ ሞት አይፈራም አይነት አማራጭ የሚመርጡ ይመስለኛል። በሁሉም አቅጣጫ በወንጀልና ከሰው ህይወት ጋር በተያያዘ ያልተነካካ የለም። እንደዚህ ገምተው እንዴት እርቅ ይቀበላሉ? እስከሚችሉት ይሄዳሉ፤ ሆኖም ግን ዴዝሞንድ ቱቱ “ያለይቅርታ የወደፊት የሚባል ነገር የለም” እንዳሉት እኔም ምንም እንኳን ሁኔታው ከባድ ቢመስልም ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ዕርቅ መሞከር ያለበት አማራጭ ነው ብዬ ለማመን እፈልጋሁ፡፡
ጎልጉልቅድም “ጉድጓዱ የራቀ ነው” ስትል አቶ መለስን እያደነቅህ ነው? አይተኩም እያልክ ነው? ወይስ…
መልስ፦ በመጀመሪያ አቶ መለስን አድንቄ አላውቅም። በብዙ ጉዳዮች የምቃወማቸውና እንደ መሪ የማልቀበላቸው ሰው ናቸው። ተዘርዝሮ የማያልቅ ታሪካዊና ሰብአዊ በደል በሚመሩት ህዝብ ላይ የፈጸሙ ሰው ናቸው። ኢትዮጵያን አሳንሰው ወደብ አልባ በማድረግ ታሪካዊ ንብረቷን በግፍ አስነጥቀዋል። ከዚህ አንጻር በህይወት ቆይተው በህግ ቢዳኙና ፍርድ ቢሰጣቸው እያልኩ የምመኝ ሰው ነኝ። ስለእርሳቸው ሳስብ ውስጤ ይቆጣል። ግን የኢህአዴግንና የአመራሮቹን ሙሉ እውቅናና “ይችላል” የሚል ማዕረግ እንዳላቸው መዘንጋት አይቻልም። ለመልካም ቢጠቀሙበት የምመኘው እውቀት እንዳላቸውም እቀበላለሁ። ግን መሪ ለመሆን የማያበቃቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። ርዕሱ ሰፊ ነው። ዋናው ጉዳይ ያለው ይህ የአቶ መለስ እውቅና ከየት መጣ? የሚለው ነው?
ጎልጉልአላደንቃቸውም ግን አይተኩም እያልክ ነው?
መልስ፦ አይደለም። አቶ መለስ ኢህአዴግ ውስጥ ሙሉ ተቀባይነት አላቸው። ይህን ተቀባይነት የፈጠሩት ራዕይ ያላቸውና አገር ወዳድ መሪ ሆነው አይደለም። ገድሎ በማዳን ነው። ገሎ በማዳን ፍልስፍናና ስልት ተክነዋል…
ጎልጉልገሎ ማዳን ምንድነው ?
መልስ፦ መለስ ስልታቸው ከገደሉ በኋላ “ላድንህ” በማለት የሚጫወቱት ጨዋታ ነው። ታምራት ላይኔ በወንጀልና በሙስና የታጠበ ሰው ነበር። ይህ ሲሆን አስቀድመው ማስቆም እየቻሉ ዝም ያሉት አውቀው ነው። መጨረሻ ላይ ግን ፓርላማ ፊት ደጋፊዎቹንና ወዳጆቹን እስኪያሳፍር ድረስ ራሱን አዋርዶ ወደቀ። ላድንህ የሚለው የመለስ ስልት ቅድመ ሁኔታው “ራስህን አዋርድና አድንሃለው” የሚል ነው ፤ አቶ ታምራት በስኳር አስመስሎ ራሱን አዋረደ። ራሱን ባደባባይ ገደለ። ከዛ ተወረወረ። የበደለውን ህዝብ ይቅርታ እንዲል ሲጠየቅ እንኳ አልቀበልም የሚለው ላድንህ ሲባል በገባው ቃል መሰረት ነው። ይህ ያለፈ ታሪክ ነው። ግን ነጻ ሆኖ እንኳ መናገር እንዳይችል የሚጫወትበትን ድንበር ሳይቀር አበጅተውለታል። ጭንቅላቱን ቦርቡረውታል። ልክ እንደ ታምራት ሁሉ በ“ላድንህ” ጨዋታ ሁሉም ባለስልጣን በበሰበሰው ስርዓት ውስጥ አብረው እንዲጨማለቁ ተደርገዋል። በነገራችን ላይ ኢህአዴግ በሰበሰ ስንል ሰዎቹን እንጂ ሌላ ግዑዝ ነገር ባለመሆኑ በመበስበስ ባህር ውስጥ እየዋኙ አሉ። ከዚህ ባህር መውጣት አይችሉም። ልክ እንደ እውነተኛው አሳ እነዚህ ሰዎች ከበሰበሱበት ባህር ውስጥ ከወጡ ስለሚሞቱ ባህሩን ከማስፋት ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም። የበስብሶ ማበስበሱ ዋና አላማ በበሰበሱበት መጠን አሽከር በመሆን የታዘዙትን ሁሉ ያለማቅማማት እንዲያከናውኑ ማድረግ ነው። ግደሉ ሲባሉ ይገላሉ። ቤተሰብህን አሳልፈህ ስጥ ሲባሉ ይስማማሉ። ከሰውነት ባህሪያቸው አርቀዋቸው እቃ አድርገዋቸዋል። ትንሽ ካፈነገጡና ሰላምታቸውን እንኳ ከቀየሩ ፋይላቸው ይከፈትና ራሳቸውን አዋርደው ይጣላሉ ወይም ይሰወራሉ። ራሳቸውን በድርጅት ግምገማ አባላትና ከፍተኛ አመራሮች ፊት “እኔ ጸረ ህዝብ ነኝ” ብለው ይረግማሉ። የሚገርመው…
ጎልጉልመለስ ራሳቸው የዘረጉት ስልት ተጎጂ ያደርጋቸዋል የሚሉ ወገኖችም አሉ፤
መልስ፦ መለስ ከትግራይም ወርደው አድዋ፣ ከአድዋም ወርደው በሰፈርና በስጋ ዝምድና ወደማመን ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በሙስና እያበሰበሱ ለመምታት የዘረጉት መዋቅር የእያንዳንዱን ባለስልጣን መረጃ ያቀብላቸዋል። ግን ርምጃ አይወስዱም። እንዲያውም አስፈጻሚዎች ርምጃ ለመውስድ ሲዘጋጁ “እረፉ” የሚል መልስ ነው የሚሰጡት። እንግዲህ በሙስና መረብ ውስጥ የተሳሰሩ ቀላል የማይባል ሃብት እንዲሰበስቡ ተመቻችቷል። በቅጽበት ከባዶ ተነስተው ባለ ሚሊዮኖች የሆኑት የገነቡት ቡድንና የፈጠሩት መረብ እንዲሁ በቀላሉ መለስ ሊጫወቱበት የሚችሉት ሃይል አልሆነም። ደግሞም…
ጎልጉል ላቋርጥህና በግልጽ መለስ ችግር ውስጥ ነበሩ?
መልስ፦ ራሱን ባመመው ቁጥር ፓናዶል መዋጥ የለመደ ሰው ያለ ፓናዶል ጤና አይሰማውም። ፓናዶል ከሌለ ራሱን ያመዋል። ፓናዶል በአገሪቱ ከጠፋ ችግሩ ይባባሳል። አቶ መለስ ለህዝብ ሳይሆን እሳቸው በፈጠሩት የበሰበሰ ባህር ውስጥ ላሉት ሁሉ እንደ ፓናዶል ይመሰላሉ። መለስ አንድ ነገር ከሆኑ ወይም መለስ አናት ላይ በቀድሞው ሃይላቸው መቀመጥ ካልቻሉ የሚታመሙ ብዙ ናቸው። ይህ አደጋ መተራመስ ይፈጥራል። እርስ በርስ እንተዋወቃለን። አሁን እንግዲህ ሁሉም ነገር አብቅቷል። መለስ አልፈዋል። ተቀብረዋል። አሁን የምናወራው ስለቀጣዩ ነው። መለስ አደጋ ውስጥ የመቆየታቸው ጉዳይ አብቅቶለታል።
ጎልጉልስለዚህ?
መልስ፦ ግልጽ እኮ ነው። መለስ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ መልክ ያላቸውን ሰዎች በልዩነት ውስጥ ይዘው ኖረዋል። ተጠቃሚ የሆኑት ክፍሎች ሃብታቸው እየገፋቸው ሳያስቡት የራሳቸውን መንግስትና አቅም ገንብተዋል። ህግና ደንብ አይመለከተንም የሚሉ ሆነዋል። ሚኒስትርና ከፍተኛ የደህንነት ሰዎችንና የጸጥታ አመራሮችን ሳይቀር እንዳሻቸው የማዘዝና የማሰማራት ደረጃ ደርሰዋል። እነዚህን ክፍሎች አክብሮና እየተንከባከቡ ከመኖር ውጪ አማራጭ የለም። መለስ ሲመሩት የነበረው ኢህአዴግ አባላቱ ሁሉ የሚያወሩት ይህንኑ ነው። ደቡብ ችግር አለ። ሙስና አለ። ፕሬዚዳንቱና ሌሎች ባለስልጣናት እስከ ቀበሌ በወረደ መዋቅር ንግድ ውስጥ ገብተዋል። ይህ ያደባባይ ሚስጥር ነው። የደቡብን ፕሬዚዳንት ለመንካት ሲታሰብ “ሲዳማ ያምጻል” ይባልና ይሸፋፈናል። ህዝብ የሚዘርፈውን መሪ አይወድም። ዝርፊያው በሰንሰለት ስለሆነ … አንዱ ጋር ከተነካ ተጓቶ፣ ተተልትሎ፣ ተስፋፍቶ መለስ ጉያ ውስጥ ይገባል። ስለዚህ ማን ማንን ይነካል። የበታች ካድሬው ይህን ያውቃል። በየግምገማው ያነሳ ነበር። ሰፊ ጉዳይ ቢሆንም መለስ ሁሌም በጉድጓዱ ጠርዝ ላይ ናቸው። ጋምቤላ፣ አማራ፣ ኦሮምያ፣ ቤኒሻንጉል… ሌብነት አለ። ትግራይ ሙስና ሰፈር አለ። ሀረሪ የውሃ ቱቦ ዘርግተናል ብለው ቦይ አስቆፍረው ቧንቧ ሳይቀብሩ አፈር መልሰው ፓርላማ “ህዝቡን ንጹህ ውሃ ልናጠጣ ነው” እያሉ ሪፖርት ያቀርቡ ነበር። ከዚህ በላይ መበስበስ ምን አለ? ስርዓቱ ስለበሰበሰ እድሜውም የመሻገቱን ያህል ነው። ሙስናውና ንግዱ አንድ ላይ ተሳስመው መጓዛቸው የስርዓቱን ፖለቲካዊ ጉልበት አሽመድምዶታል። ይህ ሁሉ መለስ ያውቁታል። በሌላ በኩል ደግሞ መለስ የገፏቸው ዋና የህወሃት ሰዎች በተለያየ ደረጃ ደጋፊዎቻቸው አሉ። የከፋውና የመረረው ህዝብም አለ…
ጎልጉልህወሃቶች ችግር ካለ አይጣሉም ብለኸኝ ነበር፤
መልስ፦ አዎ! ዝርዝር ማቅረብ አያስፈልግም። በሌላ በኩል ግን መለስ አመራሩ ላይ ስለሌሉ ያ የጋራ ነጥብ የሚባለው ነገር አይኖርም። የጋራ ነጥብ ሊሆን የሚችል የሚታመንበት ሰውም አልተዘጋጀም። ትርምሱ የሚነሳው እዚህ ላይ ነው። ፖለቲካ የሚዛን ጨዋታ ነው። አቶ ስዬ ያላቸው ተሰሚነት ቀላል አይደለም። ሌሎች በውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ንቅናቄውን አጡዘው ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ የሚችሉ አሉ። አርከበ ህወሃት ሊቀመንበር እንዲሆኑ የመረጣቸው ሰው ናቸው። እሳቸው ቢያፈነግጥ ሊንዱት ይችላል። አርከበ አዲስ አበባ “ለምን ፎቶህን ሰቀልክ” ተብለው ከህዝብ እንዲደበቁና የገነቡት ስም ሙሉ በሙሉ እንዲቆሽሽ ዘመቻ የተፈጸመባቸው ሰው ናቸው። ውጪ ያሉት የውህዳኖቹ ጥላ አለ። ይህ መላምት ከመሰለ ባጭሩ የምናገረው መለስ ሃላፊነቱን ስፍራ ላይ ስለሌሉ ስለሚሆነው ነው። ምንም ሆነ ምን ውስጥ ያሉትም ሆነ ውጭ ያሉት ህወሃቶች በመለስ መወገድ እንጂ በህወሃት መቀበር የተለያየ አቋም አላቸው ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል። ከህወሃት ጋር ጸብ የላቸውም። ጸባቸው የህወሃትን መነሻ አሰናክለው የትግራይ ህዝብ በሌሎች ዘንድ እንደ ጠላት እንዲታይ አድርገዋል ከተባሉት አቶ መለስ ጋር ነው። በየትኛውም መስፈርት ለውጥ የሚካሄድ ከሆነ በትግራይ ሰዎች ፈቃድና የበላይነት እንዲሆን የሚፈለግና እየተሰራበት ያለ ይመስለኛል። አሁንም መላምት ካልተባለ ማብራሪያ ማቅረብ ይቻላል።
ጎልጉልመለስ ከሌሉ አቻ ፓርቲዎች የመሪነት ወንበር የመያዝ የቆየ ቂማቸውን ይፋ በማውጣት ይጠይቃሉ ብለኸኝ ነበር፤
መልስ፦ አዎ። ጥያቄው መነሳቱ አይቀርም። ካድሬውና የበታች አመራሩ ድሮም ጀምሮ ሃሳቡ አለው። ግምገማ እየተባለ በሰርጎ ገቦች እየተሰለሉ እየተወገዱ እንጂ እስከዛሬም አይቆይም ነበር። ያም ሆነ ይህ መለስ ስለሌሉ የወንበር ቡቅሻው የማይቀር ነው። በየድርጅቱ አመራሮች ዘንድ የሌባና ፖሊስ፣ የሃይል ሚዛንና ቅኝት፣ አሰላለፍን የማሳመር ሰልፍ እየታየ ነው። አሁን በዝርዝር የማልናገረው አንዳንድ የመናድ ምልክቶችም አሉ። ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን ህወሃቶች የሃይል ሚዛናቸው ባለበት እንዲቀጥል የሚቻላቸውን እያደረጉ ነው። የመከላከያና የደህንነት አቅማቸውም ይህንኑ ለማድረግ ስለሚያግዛቸው የወንበር ጥያቄው እንዲሁ በዋዛ የሚከናወን አይሆንም።
ጎልጉልአቶ መለስ ልማታዊ ስለሚሏቸው ባለሃብቶች አንስተን ብንጨርስ?
መልስ፦ መጀመሪያ ስለ ባለስልጣኖች ላክል። አቶ ታምራት ለምን የሚያውቀውን ምስጢር አይናገርም? አቶ ስዬ ይምልለት ስለነበረው ስርዓትና ሲመራው ስለነበረው ኤፈርት ለምን አይተነፍስም? አቶ ገብሩ አስራት የህወሃትን ጸረ ህዝብነት ለምን ይፋ አያደርግም? በረሃ እያሉ በየዋህነት ከድርጅቱ የወጡ ወይም እነሱ እንደሚሉት “መለስን በመናቅ” ከተሸወዱት በስተቀር ስለ መለስ የሚናገሩ የሉም። ቢናገሩም ሁሉም የሚያውቀውን ተራና ጥልቅ ያልሆነ ነገር ነው። ባለስልጣናት ጥይት የማይበሳው መስኮት ያለው ቤት አስገንብተው በዶላር እያከራዩ ገንዘብ ሲሰበስቡ … ስለ ባለሃብቶች ጫናና አደገኛነት በግልጽ የሚታይ ስለሆነ በዝርዝር መናገሩ አይጠቅምም። አንድ ጄኔራል ባደባባይ ነጋዴ ሆኖ፣ ኢንቬስተር ሆኖ፣ … ሩቅ ሳንሄድ ደንበል ህንጻ የተገነባው ያለ አንዳች ማስያዣ ወይም ዋስትና በወቅቱ የልማት ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ በነበሩት አቶ ግርማ ብሩ ትዕዛዝ በተወሰደ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ነው። ጉዳዩ በጥቆማ የኢኮኖሚ ደህንነቶች ጋር ደረሰና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተወሰነ። ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ሊያደርጓቸው ሲመጡ አሁን የማልገልጸው ቦታ ሰውየው ተደበቀው ራሳቸውን ቀይረው በፖሊሶች ፊት አመለጡና ያጋጠማቸውን ለወዳጃቸው አስታወቁ። በማግስቱ ህንጻቸውን ቆመው ማስገንባት ቀጠሉ። ቆይተው ብድራቸውን መክፈል አልቻሉም ተብሎ ህንጻው በጨረታ ሊሸጥ ቀናቶች ሲቀሩ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በአንድ ቀን ውስጥ የ900 ሚሊዮንና የ600 ሚሊዮን የመንገድ ስራ ውል አጸደቀላቸው። በጋዜጦች ላይ ደንበል በጨረታ ሊሸጥ ነው እየተባለ፤ በጎን ጨረታ አሸነፉ ይባላል። ሌላው ከፍተኛ የግብር እዳ ያለባቸው አውራ ባለሃብት የግብር እዳቸውን የሚገልጽ ሰነድ እያሰረቁ፣ የሚጠሉትን ባለስልጣን እያስነሱ፣ የሚፈልጉትን እያሾሙ፣ የፈለጉትን እያሳሰሩ፣ ጥቅም ያለበትን የህዝብ ሃብትና ድርጅት ወደ ግላቸው እንዲዞር እያስደረጉ፣ የውጭ ባለሃብት ፊትለፊት እያቆሙ ያገራቸውን ባንክ የሚያዘርፉ፣ … ብዙ ማለት ይቻላል። ዞሮ ዞሮ ሁሉም ባለሃብቶች ማለት ይቻላል መለስ እንደሚሉት ሳይሆን በብስባሽ ላይ እንደሚበቅል ተክል ናቸው። ለራሳቸው እንጂ ለአገር የሚጠቅሙ አይደሉም። ያላቸው አማራጭ በመለስ ስም እየማሉ አስመስሎ የመንፈስና የይታይ ይታይ ግብር እያስገቡ ከመኖር የዘለለ አማራጭ የላቸውም። ችግር ከመጣ ያ አፉን የከፈተው ጉድጓድ እነሱን አይጠየፍም።
ጎልጉልህዝብ ለመለስ አክብሮቱን በለቅሶና በተሰበረ ሃዘን ሲገልጽ ሰንብቷል። ባለሃብቶች፣ የኪነት ባለሙያዎችና የኪነት ሰዎች… ሃዘናቸውን ገልጸዋል። የአፍሪካ መሪዎች፣ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት መለስን አወድሰዋል። ምን አስተያየት አለህ?
መልስ፦ መለስ በርካታ ስራዎች ሰርተዋል። ኢትዮጵያን የግለሰቦች መብት ሳይሸራረፍ የተከበረባት ዲሞክራሲያዊና የሰብአዊ መብት የማይጣስባት አገር አድርገው ሊመሩዋት ይችሉ ነበር። ነጻ ፕሬስ የሌለበት፣ መሰብሰብና መሰለፍ የማይቻልበት፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በነጻነት የማይንቀሳቀሱበት፣ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ መሪዎችና ደጋፊዎች የሚታሰሩበት፣ አማራጭ የሚባል ነገር የከለከሉ ሰው ነበሩ። አትሰብሰብ፣ አትናገር፣ አትቃወም፣ በዘር ካልሆነ አትደራጅ፣ የተባለና የታፈነ ህዝብ እንዴት ሃዘን ይቀመጣል? ታሪካዊና የአፋር ክልል አካል የሆነው ወደቡ የተነጠቀበት ህዝብ እንዴት እምባው ይፈሳል? በአንድ ብሄር አባላት የስለላና የወታደራዊ አፈና መዋቅር እየተረገጠ ያለ ህዝብ፣ ማዳበሪያና የርሃብ ማስታገሻ ስንዴ ለፖለቲካ መጠቀሚያ ተደርጎ በጠኔ ለሚሞቱና አንዱ መለስን ደግፎ ጠግቦ ሲያድር፣ እሳቸውን የማይደግፍ በረሃብ እየሞተ እንዴት ያለ ሃዘን ነው? የአንድ ብሄር የበላይነት ነግሶ ዜጎች በተወለዱበት ቀዬያቸው ተሸማቀው የሚኖሩት በማን መሪነትና ማን በነደፈው የአፈና መዋቅር ነው? የአሜሪካና የአውሮፓን መንግስታት በታማኝነት ማገልገል ቀዳሚ መርሃቸውና ከሽፍትነት ወደ ቤተመንግስት የተዛወሩበት ስልትም በመሆኑ ቢያወድሷቸው አይገርምም። አንድ ጥያቄ ላንሳና ልጨርስ ነፈጠኛ፣ ጨቋኝ፣ አድሃሪ፣ አስነዋሪ ተግባር የፈጸመ እየተባለ ላለፉት 21 ዓመታት የተሰደበው የአማራ ህዝብ፣ ለም መሬቱን ተነጠቆ ከትውልዱ የተፈናቀለ ህዝብ፣ ከየክልሉ ነፍጥ አንግቶ ለማስገበር የመጣ ወራሪ እየተባለ የሚፈናቀለው የአማራ ህዝብ አቶ መለስ ምኑ ስለሆኑ ደረት ይመታል? ስለምን ለመለስ ያለቅሳል? “አማራው ይደራጅ” በሚል ትግል ውስጥ ገብተው ህይወታቸው ያለፈው ፕሮፌሰር አስራት እንዲታሰሩ ለፈረደ መሪ የመንዝ ህዝብ አንድ ዘለላ እንባ እንዴት ይወጣዋል? ወልቃይትንና መተማን (ሁመራን) የተዘረፈው የአማራ ሕዝብ ሙሾ የሚያወርደው ለማን ነው? መሬት ኦነግ እየተባለ የተጨፈጨፈና አሁን ድረስ አስር ላይ የሚገኙ ዜጎች እንዴት ለአቶ መለስ ደረታቸውን ይመታሉ? ወደቡን በግፍ ሲወሰድበት ድምጹን እንኳን እንዳያሰማ የታፈነ ሕዝብ እንዴት እምባ ይወጣዋል? በጋምቤላ በአቶ መለስ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የተገደሉትና መሬታቸው የተነጠቀው አኙዋኮች እስካሁን ድረስም ልጆቻቸው እየተገደሉባቸው ያሉ እናቶች እንዴት ነው የሚያለቅሱት? ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የታሰሩ፣ የተገረፉ፣ የተገደሉ… በአገራቸው ጉዳይ “አያገባችሁም” ተብለው የተባረሩ ምሁራኖች ምን ተፈጠረ ብለው ነው ለቅሶ የሚቀመጡት? ስለተባረሩ ነው? “ከእናንተ የእኛ ካድሬዎች ይሻላሉ” ተብለው ስለተሰደቡና ስለተንቋሸሹ ነው የሚያለቅሱት? በ1997 ምርጫ ወቅት አልሞ ተኳሾች አሁንም ከአቶ መለስ በተሰጠ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ግንባርና ደረት እየመረጡ ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የደፉባቸው ሰዎች እንዴት ለቅሶ ይቀመጣሉ? አቶ መለስ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እንደመሆናቸው በእርሳቸው ትዕዛዝ የተላከው ጦር ሠራዊት በኦጋዴን ከጨፈጨፉት ወገኖቻችን በተጨማሪ አዛውንት እናቶችንና እርጉዝ ሴቶችን እንዲሁም ጨቅላ ወንዶችንም ሳይቀር አስገድደው በመድፈር አሰቃቂ ወንጀል የተፈጸመበት ህዝብ እንዴት ነው ለአቶ መለስ “ዋይ” ብሎ የሚያለቅሰው? ይህንን ጥያቄ መመለስ አግባብ ነው። ሃዘኑ በድርጅታዊ ስራ፣ ደስታው በድርጅታዊ ስራ፣ ስልጣኑ በሞኖፖል፣ የሚነግደው በውሱንና ምርጥ ዘር፣ የሚበደረው ለራሳቸው ሰው፣ የሚገነቡና የሚዝናኑ እነሱ… ሃዘኑ ግን የሁላችን!!