Monday, September 9, 2013

የሐምሌ ጨረቃ! ከአንዱዓለም አራጌ ዋለ (አንድነት ም/ሊቀመንበር ከቃሊቲ ማጎሪያ) ክፍል አንድ

ከጉልበተኞች ጠመንጃ የሚወጣ ጥይት ስጋን እንጂ እምነትን ሊገድል እንደማይችለው ሁሉ፣ ከቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ተነጥሎ ቅዝቃዜ በዋጠው ጠባብ ክፍል ውስጥ መታሰርም አካልን እንጂ ምናብን (ህልምን) ሊያስር የሚችልበት ጉልበት የለውም፡፡ ከቶስ እንደምናብ ሜዳውን፣ ተራራውን፣ ቁልቁለቱን፣ ዳገቱን፣ ሸለቆውን፣ ኮረብታውን በሰከንድ ክፍልፋዮች ከብርሃን ፈጥኖ በመምዘግዘግ ያለመዛነፍ ያሰበበት የሚደርስ ምን ኃይል አለ? ከጠባቧ ክፍል ውስጥ ‹‹ድርሻህ›› ተብላ በተሰጠችኝ 90 ሴንቲ ሜትር ላይ ቀሪ ህይወቴን አሳልፍ ዘንድ በግፍ ፍርድ ብታሰርም ዕረፍት ለማያውቀው ምናቤ ገለታ ይድረሰውና ይዞኝ ይከንፋል፤ ወደ ምፈልገው አድርሶ ይመልሰኛል፡፡


አንዳንዴ ከጁፒተር ማዶ ያሉ ተንሳፋፊ ዓለማቶችን ቢያስቃኘኝም፣ አብዛኛውን ጊዜ ግን በሀገሬ ሰማይ ስር በጥቅጥቅ ደመና ላይ አንሳፎ ታላላቅ ወንዞቿን፣ ሃይቆቿን፣ የተንጣለሉ መስኮቿንና ሰማይ ጥግ የሚደርሱ ተራሮቿን በመንፈስ ያስጐበኘኛል፡፡ በተራሮቿ ግርጌና በመስኮቿ እምብርት ላይ ችምችም ብለው የተሰሩ ጐጆ ቤቶችንና በውስጣቸው ለሺ ዓመታት በፍቅር የኖሩ ደሃ ኢትዮጵያውያንን እንደጓደኞቻቸው ከሚመለከቷቸው የቤት እንስሳቶቻቸው ጋ ይታዩኛል፡፡ በየከተሞቹ ከድህነትና ከአፈና ጋር ግብግብ የገጠሙ፣ ከድህነትና ከፖለቲካ አፈና ነፃ ለማውጣት በዓለም ዙሪያ የተበተኑ ወገኖቼን ሳይቀር በአይነ- ህሊና ያስጎበኘኛል፡፡ አንዳንዴ ውሸትን እንደብልህነት፣ አፈናን እንደ አገዛዝ ስልት የወሰዱ አሳሪ ወንድሞቼና እህቶቼ የህሊና ጓዳ ውስጥ ይዞኝ ዘው ይልና ያረበበውን እብሪት፣ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ እርስ በእርስ የሚላተሙ ሃሳቦቻቸውን ፍልሚያ… ያሳየኛል፡፡
እነዚህ ምን አይነት ኢትዮጵያውያን? ምን አይነትስ ወላጆች ናቸው? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ የምናብ ፈረስ ጋልቤ የምጐበኘው የዚህን ዘመን ክንዋኔ ብቻ ሳይሆን የተደራረበውን የዘመን ጉም እየጠራረጉ ያለፉ አያሌ ዘመናትን ወደ ኋላ አስጉዞ ያሳየኛል፡፡ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመናት፡- አክሱምን፣ ላሊበላን፣ ጐንደርን፣ ያልዘመርንለትን የገዳ ዴሞክራሲ ስርዓትንና ሌሎች የጥንት ስልጣኔዎችን በብላሽ ያስኮመኩመኛል፡፡ የኢትዮጵያን የዳር ድንበር ነፃነት ለማስከበር አባቶቻችን ያደረጓቸውን የጀግንነት ውሎዎች በተለይም የጀግንነታችን ማማና የጥቁር ህዝብ ሁሉ ኩራት የሆነውን የአድዋን ጦርነት ደጋግሜ አየዋለሁ፡፡ አድዋና መሰል የጀግንነት ማማዎች ላይ ቆሜ ኢትዮጵያውያን በየቀያቸውና በየዘመኑ ሰብዓዊ ክብራቸው ተረግጦ፣ በጭቆና አዘቅት ውስጥ ወድቀው ሲዘቅጡ ይታዩኛል፡፡ አንዳንዴ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ ልዕልናቸውንና ነፃነታቸውን ለመጐናፀፍ ያደረጉትን ትግል ያሳየኝና መንፈሴን ያበረታዋል፡፡
ታሪክ እንደሚዘክረው ከኋላ ቀሩ የፊውዳል አገዛዝ ነፃ ለመውጣት (በትክክል ወዴት ያመራ እንደነበር መናገር ባይቻልም) የመጀመሪያ አብሪ ጥይት የተተኮሰችው የ1953ቱ የእነ ጄኔራል መንግስቱና ገርማሜ ንዋይን የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራ በተደረገበት ዕለት ነው፤ አቤት! እርሱን ተከትሎ የተሻለ ንቃት ያለው ኢትዮጵያዊ በሙሉ ‹‹ሕዝባዊ መንግስት›› ለመመስረት ያሳየው እንቅስቃሴ! የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለዓመታት የሞቱለት፣ የተጋዙለት፣ የተደበደቡለት፣ የተሰደዱለት… ሰላማዊ ትግል እና ያነሷቸው ጥያቄዎች ጆሮዬ ላይ ደጋግመው አስተጋብተዋል፡፡ በወቅቱ የዘውዳዊ ስርዓት ገበሬዎች፣ ተማሪዎች፣ ሰራተኞችና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተቃውሞአቸውን በሰላማዊ መንገድ አሰምተው፣ በሰላም ወደ ቤታቸው እንዲገቡ የነበረውን ትዕግስት አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ባነፃፀርኩት ቁጥር እንደ አዲስ እደመምበታለሁ፡፡ ንጉሳዊውን ስርዓት በመቃወም ተደጋጋሚ ሰልፎች ላይ ይሳተፉ የነበሩት እና ዛሬ ለድል የበቁት የቀድሞዎቹ ተማሪዎች፣ የአሁኖቹ ገዥዎች የትምህርት ነፃነትን ከመርገጣቸውም በላይ ቅሬታ በተነሳ ቁጥር የተማሪዎች መኝታ ቤት ድረስ በመዝለቅ ደም ማፍሰሳቸውን ሳስብ፤ ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡ ንፁሃን ላይ ከውሃ ይልቅ ጥይት ማዝነብ የሚቀናቸውና ተቃዋሚዎቻቸውን በውሸት ድሪቶ ዘብጥያ የሚያወርዱ አምባገነኖች መሆናቸውን ሳስብ የማይፈታ እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡
ዘውዳዊ ስርዓቱን የተቃወሙ ሰዎች ከነገስታቱ በላይ ከዘመን ጋር የማይዘምኑ፣ ከአፈሙዝ ጋር የተጋቡ እንዴት ሊሆኑ ቻሉ? የሚል ጥያቄ አነሳለሁ፡፡ የምናብ ፈረሴ ኢትዮጵያውያን ወደዚህ ዓለም በመጣሁበት ሰሞን ከነበረው የጭቆና አገዛዝ ነፃ ለመውጣት አልመው ወደ ከፋ የአምባገነንነት ገደል የወደቁበትን የእልቂትና የዋይታ አብዮት እየደጋገመ ያስቃኘኛል፡፡ በተፋላሚዎች መካከል የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ባይኖርም አፈ-ሙዝን በአፈ-ሙዝ ለማሸነፍ የተደረገው ደም መፋሰስና ወንድም በወንድሙ አስከሬን ላይ ቆሞ የፎከረበት የእርስ በርስ ጦርነትም ሌላኛው እረፍት የሚነሳው ጉዳይ ነው፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ የግፍ ቋት የነበረውን ደርግ በኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ አሸንፎ በድል አድራጊነት ወደ ምኒሊክ ቤተ-መንግስት ሲገባ ሌላ የግፍ ቋት ይሆናል ብለው ያልጠበቁ አያሌዎች ነበሩ፡፡ ረጅሙ የመከራ ሌሊት መልሶ ላይጨልም ነግቷል ብለው ለተሻለ ነገር የተዘጋጁ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ትንሽ የሚባል አልነበረም፡፡ በአሁኑ አገዛዝ ከቀደሙት ህገ-መንግስታት የተሻለ ህገ-መንግስት ቢፀድቅም ቃልና ተግባር ሳይገናኙ ይኸው 22 ዓመታት አልፈዋል፡፡
እነሆም የሌላ ዙር የአፈና ሰለባ ሆኜ ወደምማቅቅበት እስር ቤት የምናቤ ፈረስ መልሶ አደረሰኝ፡፡ ሌላ ዙር እስር፣ ሌላ ዙር አፈና፣ ሌላ ዙር የህፃናት ለቅሶ፣ ሌላ ዙር የወላጆች ሰቆቃ፣ ሌላ ዙር ውርደት፣ ሌላ ዙር የአጤዎች ቀረርቶ፣ ሌላ ዙር የህዝብ እንባ፣ ሌላ ዙር… ባለንበት መርገጥ ቀጥለናል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የከበረና ከፍ ያለ መስዋዕትነት በመክፈል የዳር ድንበር ነፃነቱን ማስከበር ቢችልም በአገሩ ሰብዓዊ ክብሩንና ነፃነቱን ከራሱ ገዢዎች አስከብሮ መኖር የቻለበት ዘመን የለም፡፡ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ የቀጠለው የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነት ትግል በድቅድቁና ዝናባማው የሐምሌ ጨለማ የምትወጣውን ‹‹ጨረቃ›› ይመስላል፡፡ በተለይ የኤሌክትሪክ ብርሃን በሌለበት የገጠሩ የሀገራችን ክፍል የልጅነቱን የመጀመሪያ ዓመታት እንደእኔ ላሳለፈና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ትግል በአንክሮ ለተከታተለ ሁሉ ስርዓቱና ጨረቃዋ የአንድ አባት ልጆች ይሆኑበታል፡፡ የሐምሌ ወር ጨለማ ጥቁር ነው፡፡ እንደግድግዳ ፊት ለፊት ቆሞ ነፍስን ያስጨንቃል፡፡ ጫፉ የማይታይ የጥላሸት ቁልል ይመስላል፡፡ ከጨለማው መደቅደቅ የተነሳ በቅርብ እርቀት ያለ ቁስን እንኳን ለመለየት የሚያስችል ብርሃን የለም፡፡ ወደሰማይ ለሚያንጋጥጥም በጥቁር የደመና ከል የተጋረደ ነው፡፡ በዚህ መሃል ግን ህልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት የሐምሌ ወርን እየጠበቀች እየደጋገመች የምትወጣው ጨረቃም ወቅቷን ጠብቃ መውጣቷን አላቋረጠችም፡፡ ከአንድ ጥቁር የደመና ኮረብታ ወደሌላው ስትወረወር ለቅፅበት ትንሽ ብርሃን ብትፈነጥቅም ምድሩን እንደቡልኮ የሸፈነውን ድቅድቁን ጨለማ ሰንጥቆ ለማለፍ የሚችል የብርሃን ፍንጣቂ በመልቀቅ የጨለማውን ሀይል መግፈፍ የሚችል አቅም የላትም፡፡ እንዲያውም በብርሃን ጅረት የተሞላው መላ አካሏ በጨለማው ፅልመት ጠልሽቶና ከጨለማው ጋር ተመሳስሎ ይታያል፡፡ የሐምሌ ጨረቃ ወይ ድቅድቁን አትገፋ፣ ወይም የሐምሌን ወር አትዘል በየዘመኑ፣ በየአመቱ ፍሬ አልባ ዑደቷን ቀጥላለች፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልም እንዲሁ፡፡ እንደ ሐምሌ ጨረቃ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብም የሀገሩን የህላዌ እድሜ ያህል ከጭቆናው ሌሊት ጋር በየወቅቱ ግብግብ ይገጥማል፡፡ በተለይም ከ1953 ዓ.ም ወዲህ ያሉት 50 ዓመታት ህዝባችን ከአብራኩ ከወጡ አምባገነን ገዥዎች መዳፍ ነፃ ለመውጣት ተደጋጋሚ ትግል አድርጓል፡ ፡ አሁንም እያደረገ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሰብዓዊ ልዕልናው ባለቤት ለመሆን የሚያስችለውን የተጠና፣ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት የሚመራና ህዝብ የራሱ ያደረገው የፀና ሰላማዊ ትግል በማድረግ ለውጤት አልበቃም፡፡
ለምን? በረጅሙ የሀገራችን ታሪክ የሀገርን ዳር ድንበር ማስከበርን የመሳሰሉ ገንቢ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ፍልስፍናዎች ማዳበር የመቻላችንን ያህል፤ በሌላ መልኩም አሉታዊ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ፍልስፍናዎች እንዳዳበርን መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ፖለቲካዊ መስተጋብራችን የተፋለሰ እንዲሆን አስተዋፆ አድርገዋል፡፡ በተለይም ከዘመነ-መሳፍንት በኋላ ያለውና በዚያ ዘመን የፖለቲካ ብሒል የተቃኘው ፖለቲካዊ ፍልስፍናችን ከምህዋሩ የወጣ ነው፡፡ በአመዛኙ በፍርሃት፣ በአድርባይነትና በጊዜያዊ ጥቅም የተለወሰ ፍርሃት፣ የማያምኑበትን መናገር፣ በአርምሞ ማሳለፍ፣ ያልሆነውን ሁነን መታየት፣ ነገሮችን በሚስጥር መያዝ፣ ተጠራጣሪነትና በውል ባልታሸ ሁኔታ እራስን ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ማራመድ የመሳሰሉትን ለአብነት ያህል ማንሳት ይቻላል፡፡ በየዘመኑ የሚነሱ አምባገነኖችና የጎበዝ አለቆች ጥላ ስር ለመጠለል መሞከር እነርሱን አይነኬ አድርጐ መቁጠር እራስን ፍፁም አቅመ-ቢስ አድርጐ መረዳት ለገዥዎች ማሸርገድና ቅዳሴ-ማህሌት መቆም አያሌ ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ እንደ ፖለቲካ-ጥበብ የሚቆጥሩት አካሄድ ነው፡፡ ይህም ሁሉ በጥልቅ አስተሳሰብና ከዚያም በሚመነጭ እምነት ላይ ቢመሰረት ችግር አልነበረውም፡፡ የተሳሳተ እምነት በማንገብ የጨለማ አገዛዞችን የነፃነት ንጋት ናቸው ብለው የሚዘምሩ፤ በረሃብ ስንሞት በቁንጣን ነው ብለው ሊያሳምኑን የሚዳዳቸው፤ የአገዛዞች ዋልታና ማገር የሆኑ ኢትዮጵያውያንን በየዘመኑ አይተናል፡፡ እያየንም ነው፡፡
ከዘመናት የአፈና አገዛዝ ነፃ ልንወጣ ይገባናል ብለን የምንታገል ወገኖች እንደመኖራችን ሁሉ፤ አገዛዙ የፀሐይ መውጫ ምኩራብ ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች እምነታቸውን ያራምዱ ዘንድ መብታቸው ነው፡፡ ከስሜታዊነት በፀዳ መልኩ ጨለማው በእርግጥም ጨለማ መሆኑን አይኖቻቸውን ገልጠው እንዲያዩና እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል፡፡ ሞታችን ከጨለማው ጋር ነው ብለው በጨለማው አካልነታቸው መቀጠል የሚፈልጉ ከሆነ ደግሞ ታግሎ ማሸነፍና እነርሱም ከጨለማ ነፃ እንዲወጡ ማድረግ ነው፡፡ ከባዱ የቤት ስራና እስከአሁንም ነፃነት ከእኛ እንዲርቅ ትልቁን አስተዋፆ እያበረከተ ያለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ‹‹መሃል ሰፋሪው›‹› ኢትዮጵያዊ ይመስለኛል፡፡ እውነቱን ለመናገር በፖለቲካ ትግል ባሳለፍኳቸው ጥቂት ዓመታት ከባዱ ፈተና የገጠመኝ ከቤተሰቤ፣ ከወዳጆቼና ከቅርብ ጓደኞቼ ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ እነዚህ ወገኖች ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ ከአገዛዙ ጋር ግብግብ ከመግጠም ይልቅ አንገቴን ደፍቼ ልጆቼን እንዳሳድግ ምክራቸውን በተደጋጋሚ ለግሰውኛል፡ ፡ ለነገሩ ትዳር ባልያዝኩበት፣ ልጆች ባልነበሩኝ ወቅትም ‹‹አርፈህ ተቀመጥ!›› የሚለው ምክራቸው አልተለየኝም ነበር፡፡ ትግል ውስጥ እንዳልገባ የሚሰጡኝ ምክንያቶች ሁለት ናቸው፡፡ የሀገራችን ፖለቲካ በደም መፋሰስና በሸፍጥ የተሞላ መሆኑ አንደኛው ሲሆን በተጨማሪም ከኢኮኖሚ አዋጭነት አንፃር ፖለቲካ ፈፅሞ የማይመከር መሆኑን ያስረዱኛል፡፡ በመሆኑም አንገቴን ደፍቼ፣ ገዥዎች ወደአጋዙኝ ተግዤ እንድኖር፤ ልጆቼንም እንዳሳድግ ምክራቸውን ለግሰውኝ ነበር፡፡ አሁን እንኳን በእስር ላይ እያለሁ እንደሳይቤሪያ ብርድ አጥንትን ሰብሮ የሚገባና ነፍስን የሚወጋ ምክራቸውን ይልኩልኛል፡፡ ‹‹ነግረነው አልሰማንም››፣ ‹‹ህፃናት ልጆቹን ያለአባት ትቶ እንዴት ይታሰራል?›› ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከመበሳጨታቸው የተነሳ የመጐብኘት መብቴ ቢከበር እንኳን ሊጐበኙኝ እንደማይፈልጉ ይናገራሉ፡፡ ወንጀልሰርቼ እንዳልታሰርኩ፣ ለመስራትም እንደማላስብና ሰላማዊ የትግል ስልትን የሃይማኖት ያህል እንደማምንበት ወዳጆቼም ሆኑ አሳሪዎቼ እኔ የማውቀውን ያህል ያውቃሉ ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡
ያም ሆኖ ግን ወዳጆቼ ስርየት እንደሌለው ሃጢያት፣ የአገዛዙ ዋናዎችም የሰማይስባሪ እንደሚያክል ወንጀል የቆጠሩት የተቃውሞ ፖለቲካ ጐራ መቀላቀሌን፣ በሀገሬ አንገቴን ቀና አድርጌ በመራመዴና የማምንበትን በቀጥታ በመናገሬ ነው፡፡ አገዛዙም ይኽን አይነት በፍርሃት የተሸበበ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ይፈልጋል፤ ወዳጆቼም አገዛዙ በግፍ ስላሰረኝ የነቢይነት ደረጃቸውን በመደመምያስባሉ፤ እርስ በእርሳቸው ይመጋገባሉ፡፡ የትችት ጦራቸውን እስር ቤት ድረስ የሚወረውሩት አብዛኞቹ ጓደኞቼ በታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች የተማሩና የሚያስተምሩ፣ በመደበኛ ትምህርት ልህቀታቸው በሊቀ- ጠበብትነት ጐራ የሚሰለፉና ይህች ደሀ አገር ከውስን ጥሪቷ ቆንጥራ ያስተማረቻቸው ናቸው፡፡ የሆነ ሆኖ ዛሬ ወዳጆቼ ያሉት ደርሶብኛል፤ ትንቢታቸው ሰምሯል፡፡ አዎ! ልጆቼ በድንገት ከቤት ወጥቶ እስከአሁን ወደቤት ስላልተመለሰው አባታቸው በህፃንነት የአእምሮ ጓዳቸው ውስጥ እያንሰላሰሉና እየተጐዱ መሆኑን በሚገባ እረዳለሁ፡፡ በተለይ ልክ የታሰርኩ እለት የትምህርት ቤትን ደጃፍ የረገጠው የልጄ የሩህ ጥያቄዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየበረከቱ መጥተዋል፡፡ ‹‹ማሚ፣ እኔ አባት የለኝም እንዴ?››፣ ‹‹አባባ መቼ ነው ቤት የሚመጣው?››፣ ‹‹የአንተ ስራ መቼ ነው የሚያልቀው?›› የሚሉ ናፍቆት ያንገበገባቸውን ጥያቄዎች ያነሳል፡፡
እኔ የምከፍለው ዋጋ ይቅርና ልጆቼም በውል በማይረዱት ነገር ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን በጥሞና እገነዘባለሁ፡፡ ቀድሞውንም ያልጠበኩትም አልነበረም የሆነው፡፡ ግና! በልጆቼ ሰብዕና ላይ የከፋ ስብራት እንዳይደርስ እውነተኛ ፈራጅ ወደሆነው ፈጣሪ ከመፀለይ በቀር ምን ማድረግ ይቻለኛል? ይህችን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀለው በእስር ቤት ነው፤ ይኸው አሁን ደግሞ ባልጠኑ እግሮቹ፣ ክፉ ደግ ባለየ ህሊናው ከሚያፈቅረው አባቱ ተለይቶ በባዕድ ምድር የፖለቲካ ስደተኛ ሆኖ የሚንከራተተው የናፍቆት እስክንድር ነጋ ህይወት ለዚህ የበቃው አባቱ እንደኔ የወዳጆቹን የአርምሞ ጥያቄ ባለመቀበሉ ጭምር ነው፡፡ አባታቸውን ተመላልሰው መጠየቅ በማይችሉበት እርቀት ላይ የታሰረባቸው የናትናኤል መኮንን ልጆች እንባም ሰብዓዊ ፍጡርን በተለይም የወላጆችን ልብ ምንኛ እንደሚሰብር ግልፅ ነው፡፡ ከሚያስተምርበት አዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከግቢ ውጭ እንደሚፈለግ በስልክ ሲነገረው የጠመኔውን ብናኝ ከእጁ ላይ አራግፎ የወጣው የኦሮሞ ፌዴራሊስ ኮንግረስ /ኦፌኮ/ ም/ሊቀመንበር በቀለ ገርባ ‹‹የኦነግ አባልና የፌደራላዊ አገዛዙን በኃይል ማስገንጠል አሲረሀል›› በሚል ክስ ተፈርዶበት ከህፃናት ልጆቹ ተለይቶ በዝዋይ እስር ቤት የግፉን ፅዋ እየተጎነጨ ነው፡፡ በእርግጥ አቶ በቀለም እንደ እኛ አርፎ ልጆቹን እንዲያሳድግ ተነግሮት ነበር፡፡ ሌሎች አያሌ ኢትዮጵያውያንና ልጆቻቸውም ተመሳሳይ የመከራ ህይወት እየገፋ ይገኛሉ፡፡ ልጆቻችንና የትዳር አጋሮቻችን እየከፈሉ ያሉት ዋጋ እኛ በእስር ቤት ከምንከፍለው የከፋ ይመስለኛል፡፡
ለጓደኞቼና ለወዳጆቼ የማነሳላቸው ጥያቄዎች ይኖሩኛል፡፡ ነፃነት አልቦ ህይወት ምን ምን ይላል? ለመሆኑ ነፃነትን በገዥዎች ችሮታ የተጐናፀፈው የየትኛው ሀገር ህዝብ ነው? በየትኛው ክ/ዘመን ይሆን? …አባቶቻችን ዳር ድንበራቸውን ለማስከበር ልጆቻቸውን፣ ሚስቶቻቸውንና ዘመድ አዝማዶቻቸውን ከኋላቸው ጥለው ወደ አድዋ መዝመታቸው ስህተት ነበር እያላችሁን ይሆን? ቴዎድሮስ በመቅደላ፣ ዮሐንስ በመተማ ለሀገር ክብር መውደቃቸው ትርጉም የለሽ ነበር ማለት ነው? ሌሎች አባቶቻችንስ በጉራ፣ በጉንደት፣ በማይጨው እና በአያሌ የጦር አውድማዎች ለሀገር ክብር እንደወጡ ሲቀሩ የሚናፍቋቸው ሚስቶችና የሚሳሱላቸው ህፃናት ልጆች ያልነበሯቸው ይመስሏችኋል? አሉላ አባ ነጋ እስከ እርጅና ዘመኑ ድረስ ለሀገሩ ዳር ድንበር አጥር ሆኖ ጣሊያንና ግብፅን በማስጨነቅ ዛሬ የምንኮፈስበትን ታሪክ ማጐናፀፉ ስህተት ነበር እያላችሁ ይሆን? የእነ በላይ ዘለቀ፣ የእነ አብዲሳ አጋ፣ የእነዘርአይ ደረሰ፣ የእነ ራስ ደስታ ዳምጠው፣ የእነ አቡነ ጴጥሮስና የሌሎችም ስመ-ጥር ጀግኖቻችን ውሎ በከንቱ ጀብደኝነትና ግብታዊነት የተሞላ ነበር ማለት ነው? እነዚህ ጀግኖች የሀገራቸውን ዳር ድንበር ክብር ለማስጠበቅ ከቀያቸው ርቀው ሲጓዙ ሞትን ከፊት ለፊታቸው እያዩት የቆሙለት እውነት አመዝኖባቸው እንደነበር ዘንግታችሁት ይሆን? አባቶቻችን በየተራራውና ኮረብታው ስለሀገር ክብር ባይቀበሩ ኖሮ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ማግኘት የምንችል ይመስላችኋል? ወይስ የዳር ድንበር ነፃነት ከተከበረ፣ ዜጐች በጭቆና ቀንበር ቢማቅቁ ምንም ክፋት የለውም እያላችሁ ነው? ወይስ ጭቆና ከአብራካችን በወጡ ሰዎች እስከሆነ ድረስ እንደክብር ይቆጠራል እያላችሁ ነው? የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር የተከፈለው ዋጋ ጠጋ ብለን ስናየው የህዝብን መሰረታዊ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደሚያነሳ ሳታችሁት? አባቶቻችን ለሀገር ነፃነት የከፈሉት ዋጋ ተገቢ አልነበረም ካላላችሁ በስተቀር ለዜጐች ሉዓላዊነትና ለዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መታገል ስህተት ሆኖ የሚገኘው በምን ቀመር ነው? በዩኒቨርስቲዎች ስለ- ሰብዓዊ ፍጡር ልዕልና የምትማሯቸውና የምታስተምሯቸው ትምህርቶች ‹ነፃነት›ን በተመለከተ ምን ነበር ያሏችሁ? ወይስ ዲሞክራሲና ነፃነት ለእኛ ሀገር አይሰራም እያላችሁ ነው? የጥቁር ህዝብ ኩራት የሆነውን የአድዋን ድል ያስመዘገቡ አባቶች ልጆች ሉዓላዊነታችን ከገዥዎቻችን መዳፍ ነጥቀን ማስከበር ካልቻልን ‹የእሳት ልጅ አመድ› መሆን አይመስላችሁም? ሌላው ቢቀር ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛትን ቀንበር እንዲሰብሩ የረዳቻቸው የአፍሪካ አገሮች በዴሞክራሲ ጐዳና በርቀት ጥለውን ሲተሙ፤ የእኛ በጭቆና አረንቋ ውስጥ መዳከር እንዴት ቁጭት አይፈጥርባችሁም? ወይስ የእናንተ ድርሻ ትችትና ታዛቢነት ብቻ ነው? እነዚህ ከፍ ብዬ ያነሳኋቸው ጥያቄዎች ለምወዳቸው ጓደኞቼ ብቻ ሳይሆን ‹‹የመሃል-ሰፋሪነት›› ሚና ለመረጡ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሁሉ የተሰነዘሩ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ ባህላችን ውስጥ ያሉ ሸንኮፎችን አስቀድመን መግረዝ ካልቻልን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል እንደ ሐምሌዋ ጨረቃ አሁንም በከንቱ ብቅ ጥልቅ ከማለት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡ ፡ ምናልባት የሀሳባችሁ ማጠንጠኛ ባለፈው ግማሽ ምዕተ-ዓመት ማሳካት ያልተቻለው እንዴት አሁን ይቻላል? የሚል ከሆነ ይኸንን ጥያቄ ማንሳት፣ ለጥያቄውም መልስ መስጠትና በመልሱም ላይ ተመስርቶ በእውነተኛ ነፃነትና ህዝባዊ ልዕልና ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መታገል እንደሚያስፈልግ መተማመን ላይ መድረስ ይጠበቅብናል፡፡ የተወሰኑ ጥያቄዎችን አክዬ ላንሣ፡ ፡ ሁሉም የግል ጥቅሙንና የአብራኩን ክፋዮች ብቻ በሚያስቡባት ሀገር እንዴት ህዝብ ከአገዛዝ ነፃ ሊሆን ይችላል? በየማጀቱ አገዛዙን በመርገም ነፃ መውጣት ቢቻል ኑሮ ከረጅም ዘመናት በፊት ነፃ አንወጣም ነበር ትላላችሁ? አባቶቻችን ለነፃነት መስዋዕት መሆናቸው ትክክል ነበር የምትሉ ከሆነ የስብዕና መሰረትና የነፃነቶች ሁሉ የበላይ ለሆነው የሰብዓዊ መብት መታገል ትክክል የማይሆንበት አሳማኝ ምክንያት ምንድን ነው? ከገዥዎች መዳፍ ለመውጣት አሳማኝ ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? ይኽን ከገዥዎች መዳፍ ለመውጣት የሚደረግን ትግል እንዳላየን አይተን ብናልፍ ለሁላችንም የማይቀረው ሞትን ተጋፍጠን ወደመቃብር ስንወርድ በምን አይነት ክብርና የህሊና እረፍት ማሸለብ እንችል ይሆን? የዘወትር ህልማችን ሰብዓዊ ልዕልናችን ተጠብቆ የምንኖርበትንና ልጆቻችን የማያፍሩበትን ሀገር ማውረስ ሆኖ ሳለ የአገዛዙን የጭቆና አርጩሜ በመፍራት ከእምነታችን ውጭ የሆኑ ተግባሮችን ስንፈፅም የምንበጀው እስከመቼ ነው? ለዘመናት እላያችን ላይ ቤት የሰራብንን የጭቆና ቀንበር መስበር በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያልተከወነ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲንከባለል የመጣ የቤት ስራ ነው፡፡ በውዝፍ ያደረ ቁምነገር ከቅርሶቻችን ሁሉ የገዘፈና የታሪካችን ፈርጥና የማንነታችንም መደምደሚያ ነው፡፡ በዚህ የሰብዓዊ ልዕልና ጉዳይ ላይ መታገል ሰው የመሆንና ያለመሆንን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ በነፃነት አለመታገል የቤት ስራውን ለልጆቻችን ወዝፎ ማሳደር በጭቆና ቀንበር ለመገዛት ህዝበ ውሳኔ የመስጠት ያህል ይቆጠራል፡፡ በሌላ በኩል ነፃ ለመውጣት እንደቀድሞ ነፃ አውጭ አበጋዞችን መጠበቅ አይገባንም፡፡ ይኽን የምናደርግ ከሆነ ሰማያችን በጭቆና ደመና እንደተሸፈነ ይቀጥላል፡፡ ጥቂቶችን አንጋጠን ስንጠብቅ በውስጣችን ያለውን ትልቅ የነፃነት ሃይል እንዳናይ ግርዶሽ ይሆንብናል፡፡
ይኽን በመሰለው የነፃነት ትግል የሚጀምረው የራስን የከረመና የተሳሳተ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አስተሳሰብ ከመሞገት ነው፡፡ ከዚያም ከፍ ሲል እንደ ፖለቲካ ባህልና የብልህነት ቁንጮ በመውሰድ ለህፃናት ልጆቻችን ሳይቀር በምክር መልክ የምንለግሳቸው ልዩ ልዩ ያልተሰለቀቁ አሉታዊ አስተሳሰቦችን በቅድሚያ ታግሎ መጣል ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ስለሁሉም ፤ሁሉም ስለእያንዳንዱ ግድ በማይሰጠው ሀገር ውስጥ አምባገነኖች የሚዘውሯቸው አገዛዞች መኖራቸው የግድ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ስለነፃነት ክብርነት ለማንም ማስረዳት እምብዛም አይጠበቅብንም፡፡ ነፃነት እንደ እንጉዳይ በየዛፉ ስር ያለትልቅ መስዋዕትነት በቅሎ የሚገኝ አይደለም፡፡ ይኸንን የነፃነትን ውድነት ስንረዳ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር እንደዘመቱት አባቶቻችን ሁሉ ያለነፃነት ከመኖር ይልቅ ህፃናት ልጆቻችን ጥለን፣ ከሞቀ ቤታችን ወጥተን በእስር ቤት የሲሚንቶ ወለል ላይ መጣልን እንመርጣለን፡፡ በነገራችን ላይ ደጋግሜ ከምጠቅሳቸው ጀግኖች ጋር እራሴን እያወዳደርኩ አለመሆኑን አንባቢዎች ልብ እንድትሉልኝ እወዳለሁ፡፡ በታሪክ ኮረብቶች ላይ ከድንቅ የጀግንነት ውሎዎቻቸው ጋር ከፍ ብለው የሚታዩ ጀግኖች ጫፍ የሚደርስ አንዳች ስራ እንዳልሰራሁ ጥሩ አድርጌ እገነዘባለሁ፡፡ አላማዬ የዳር ድንበርን ሉዓላዊነት ከሰብዓዊ ሉዓላዊነት ጋር ማነፃፀር ነው፡፡
ሌላው የአገር ውስጥ ገዥዎችንን እንዴት ከውጭ ሀገር ወራዎች ጋር ያነፃፅራል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ሁለቱም የዘመቱት በነፃነታችንና ሰብዓዊ ክብራችን ላይ ነው፡፡ የነፃነት ትርጉም ከሀገር ልጅነትም በላይ ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል መንገድ ስንጓዝ ትግላችን ጨቋኝ ወንድሞቻችን ወደልባቸው እንዲመለሱና ሁላችንም በነፃነት የምንኖርባትን የጋራ ሀገር እውን እንድትሆን ከማድረግ ጋር ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ እንዲታመሙና እንዲሞቱ አይደለም ፡፡ በእኛና በልጆቻችን ላይ እያደረሱት ያለው በደል በእነርሱም ላይ እንዲደርስ ፈፅሞ የምንመኘው ነገር አይደለም፡፡ ነ ፃነትን ከውጭ ሀገር ወራሪም ሆነ ከሀገር ውስጥ ጨቋኝ መጠበቅ መቼም በይደር የሚያዝ ተግባር አይደለም፡፡ ስለሁላችን ነፃነትና ሉዓላዊነት የተዘረጋ የተማፅኖ ቃል እንጂ፡፡ በሀሰት ‹‹አሸባሪ›› ተብለን ዘብጥያ ብንወርድም ትግሉን ከመቀጠል ውጭ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ነፃነትን መጠየቅና መታገል ነፃነቱን የተጠማ የነፃነት ታጋይ ሁሉ ድርሻ መሆን ይኖርበታል፤ ይሁንና የናፈቃችኋትን ነፃነት አታገኟትም ብለው ወህኒ መወርወር የአፋኞች የአፈና ተግባር ቢሆንም መንበርከክ ለከፋ መከራ፣ ለበረታ ጭቆና ከማገለጥ ውጪ ትርፍ አልባ ነው፡፡ የአሁኖቹ ገዥዎች እንደ ቀድሞዎቹ ሁሉ የተሳሳተ የፖለቲካ ባህላችን ያበቀላቸው መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ የፖለቲካ ባህላችንና አስተሳሰባችን ካልተቀየረ እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ ሌሎች አምባገነኖችንም ማብቀሉን ይቀጥላል፡፡
በአምስት አመት ውስጥ ማዕከላዊ እስር ቤት ሁለት ጊዜ ስታሰር፤ ሃላፊዎች ተለዋውጠው ባገኛቸውም የሁለቱም ዋና ኃላፊዎች ቃልና ተግባር ግን ትንሽ እንኳ ልዩነት አልነበረውም፡፡ በሚገርም ሁኔታ ሁለቱም እንዳገኙኝ የጠየቁኝ አንድ አይነት ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹ወንድ ከሆንክ ለምን ጫካ አትገባም?›› የሚል፡፡ ወንድነት ማለት አፈ-ሙዝን፤ በማይናወጥ የፍቅርና የወንድማማችነት መንገድ መጋፈጥ፤ ተጋፍጦም ሳይገሉ መሞት ነው ወይንስ በራሳችን ጥላ ሳይቀር እየደነበርን ንፁሃንን መግደል? የሚገርመው እኮ ለአፈ-ሙዝ ፍልሚያ የጥሪ ካርድ የሚበትኑት ወገኖች የደሃ ኢትዮጵያውያን ወንድማማቾችን ደም ለማፍሰስ እንጂ እነርሱማ ከመኪና ተደግፈው ለመውረድ ምንም የማይቀራቸው ናቸው፡፡ አንዳንድ በተለይም የአገዛዙ ዋነኛ ሰዎች ይችን ሀገር ለሁላችን ወደሚበጅ ንጋት ይዘዋት ለመውጣት እድሉን ለዓመታት ቢያገኙም ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ ይልቅስ እብሪት የሁለንተናቸው ማጠንጠኛ ምህዋር ሆኖአል፡፡ አንዳንዶቹን በጨረፍታ በማየት ለወንድማማችነትና የኢትዮጵያን የባጁ ችግሮች ለመፍታት በጐ አስተዋፆ ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል፣ ሕዝብን እንኳን ባይፈሩ ፈጣሪን ይፈሩ ይሆናል ብለን ተስፋ ብናደርግም ሁለቱንም እንደማይፈሩና የኢህአዴግ ዋና ሰዎች መለያ የሆነውን እብሪትና ሃኬት የሙጥኝ ብለው መንጐድ ቀጥለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ አገዛዞች ከዚህ የተለየ ሲያደርጉ አልታዩም፡፡ ይኸኛው አገዛዝ ከቀድሞዎቹ ለመለየት የሚሞክረው በእውነት ላይ ያልተመሰረተ የፕሮፓጋንዳ ደመራ በማቀጣጠል ነው፡፡ የፕሮፓጋንዳ ደመራው ህዝቡንም ሆነ አገዛዙን በብርሃን እንዲመላለስ አላደረገውም፡፡ ሊያደርገውም አይችልም፡፡ አገዛዙም ሆነ ህዝቡ ከፍርሃትና ከጨለማ ጉዞ ነፃ ሊወጣ የሚችለው የእውነት ችቦ ለኩሶ ከዚያም በሚገኘው ብርሃን ዙሪያ ተሰባስቦ መወያየት ሲቻል ነው፡፡ ለዜጐች ሉዓላዊነት ክብር የሚሰጥ አገዛዝ ቢኖር የፕሮፓጋንዳ ደመራ አቀጣጥሎ በዙሪያው መጨፈር ባላስፈለገ ነበር፡፡ ምክንያቱም ተግባር ከቃላት በላይ ይናገራልና፡፡ የአገዛዙን አምባገነናዊ ባህሪዎችና ተግባሮች በመተንተን ከዚህ በላይ ጊዜ ልናጠፋ አይገባንም፡፡ ምንስ የማይታወቅ ነገር አለ? እንኳን የአፈናው ሰለባዎች ኢትዮጵያውያን ቀርቶ ዓለምም በቅጡ ተረድቶታል፡፡ አገዛዙ ለህዝብ ፈቃድ የሚገዛ ቢሆን ለመቃወም ከቤታችን መውጣት ባላስፈለገን ነበር፡፡
ትልቁ መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ከ50 ዓመታት በላይ የአገዛዝ ስርዓትን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዋር ለማስወገድ የተደረገው ጥረት፣ የተከፈለው የህይወትና የአካል መስዋዕትነት እንዴት እስካሁን ለፍሬ ሊበቃ አልቻለም? የሚለው ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እስከ አሁን ቢያንስ ወደተሻለ ምዕራፍ ትግሉን ለማሸጋገር አልቻሉም? እስከ አሁን በተደራጁ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ገብቶ ከመታገል ይልቅ በተለየና የራሳችን በሆነ መንገድ አስተዋፆ እናበረክታለን ብለን በተለያየ መስክ ተሰልፈን የምንገኝ ሰዎችም ምን ያህል አስተዋፆ አበረከትን? ብለን ራሳችንን መፈተሽ ይገባናል፡፡ ጊዜው በተግባር የማይደገፍና የተጠጋገኑ ምክንያቶችን በመደርደር ብቻ ከተጠያቂነት የምናመልጥበት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን የአፈናው ሰለባዎች መሆናችንን አለም በቅጡ ተረድቶታል፡፡ አገዛዙ ለህዝብ ፈቃድ የሚገዛ፣ የህግ የበላይነትን የሚያከበር ቢሆን ኖሮ ለመቃወም ከቤታችን መውጣት ባላስፈለገን ነበር፡፡ ትልቁ መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ከ50 ዓመታት በላይ የአገዛዝ ስርዓትን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዋር ለማስወገድ የተደረገው ጥረት፣ የተከፈለው የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ዛሬም ለፍሬ ሊበቃ ያልቻለበትን ምክንያት ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችስ ስለምን ትግሉን ወደተሻለ ምዕራፍ ማሸገር ተሳናቸው? ዛሬም ድረስ የተደራጀ የፖለቲካ ትግልን ተቀላቅሎ ከመታገል ይልቅ በተለየና የራሳችን በሆነ መንገድ አስተዋፆ እናበረክታለን ብለን በተለያየ መስክ ተሰልፈን የምንገኝ ሰዎችም አበርክቶአችን ምን ያህል እንደሆነ ራሳችንን መፈተሽ ይገባናል፡፡ ጊዜው በተግባር የማይደገፍና የተጠጋገኑ ምክንያቶችን በመደርደር ብቻ ከተጠያቂነት የምናመልጥበት አይደለም፡፡ የነፃነት ጉዳይ ‹ለነገ…› ተብሎ በይደር የሚቆይ አይደለም፡፡