Sunday, October 6, 2013

ወያኔን ለማስወገድ አስገዳጅ የትግል ስልት ወሳኝ ነው!!!

ከለምለም አንዳርጌ(ኖርዌይ)

ላለፉት ሁለት አስርተ አመታት ኢትዮጲያና ሕዝቦ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ይህ ነው የማይባል ግፍና ሰቆቃ ሲፈጽም የኖረው የዘረኛው የወያኔ ስርዓት የእድሜ ዘመኑ ማብቂያ ጠርዝ ላይ ለመሆኑ ኢትዮጲያን ያህል ሃገርና ህዝብ ከሚመራ ስርዓት የማይጠበቁ የማፍያ ተግባራቱ ስርዓቱ ያለበት የዝቅጠት ደረጃ ጠቋሚዎች ናችው፡፡ በእድሜ ዘመን መጀመሪያ በስም እንጂ በተግባር ዴሞክራሲን የማያቀው የአንድ ጎጥ ቡድን ለይስሙላ ባስቀመጠው ህገ-መንግስት የተካተቱትን የዜጎችን መብት በመሻር ሃገሪቱን የምድር ሲኦል አርገዋታል፡፡ በሃገሪቱ ህገ-መንግስት መሰረት መብታቸውን አውቀው የተቋቋሙ የሞያ ማህበራትም ሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች በራሳቸውም ሆነ በስርዓቱ ተጽእኖ ይህ ነው የማይባል ተግባራት ሳይከውኑ በዘረኛው ስርዓት እየተኮረኮሙ ይፈርሳሉ አልይም በሞኖፖል በተያዘው የፍትህ ስርዓት ተወንጅለው በግፍ በእስር  ይማቅቃሉ፡፡
ከአመታት በኋላ ፍርሃታቸውን አሸንፈው የወያኔ መናጆ መሆን ይበቃናል ብለው ህገ-መንግስቱ የሚፈቅድላቸውን መብት ለመጠቀም ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ወያኔን እምቢኝ እያሉ ያሉት በአገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉት ጥቂት የፖለቲካ ድርጅቶች መብታቸውን ተጠቅመው የሚያደርጉት የሰላማዊ ትግል መርህ የዚህን ዘረኛ ስርዓት ማንነት ፍንትው አድርጎ ያሳየን አጋጣሚ ነው፡፡ ምንም እንኳን የኢትዮጲያ ሕዝብ ስለወያኔ ማንነትና ምንነት የጠለቅ ግንዛቤ ቢኖረውም በዚህ ደረጃ በወረደና በዘቀጠ ማፊያ ቡድን እንደምንመራ ማመን በእጅጉ ይክብዳል፡፡

አንድ የፖለቲካ ድርጅት እንደ ድርጅት ምልኡ የሚሆነው የተነሳለትን አላማና እቅድ እንዲሁም የሕዝብን መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ እንዲያገኙ በፅናት መታገል ሲችል ነው፡፡ እንደ ወያኔ ያለ አምባገነን ስርዓት አፍኖ ለያዘው የሕዝብ የመብት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው በተፅኖ እንጂ በችሮታ አይደለም፡፡ ለሚጠየቀው ህገ መንግስታዊ የሕዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ አይጠበቅም አምባገነን ነውና፡፡ ስለሆነም መብቱን የሚያስከብር  ለምን?! እን?! በቃኝ፣! እምቢ! የሚል የሕዝብ አደረጃጀት እንዲኖር የፖለቲካ ድርጅቶች በተገቢው ደረጃ ሕዝብን ማደራጀትና መርሆና፣ እቅዳቸውን ማስረፅ እንዲሁም ለለውጥ የተዘጋጀ ትግሉን ከዳር ሊያደርስ የሚችል ፍርሃቱን የሰበረ የህብረተሰብ ሃይል ሊገነቡ ግድ ይላቸዋል፡፡
ይህንን ህዝብ ለትግል በማነፅ የግፍ ቀንበሩን  ከጫንቃው ላይ ማውረድ የሕዝብ  ወገን ነን ከሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ የትኛውም የትግል ስልት አይነቱ ይለያይ እንጂ ቁርጠኝነትና መስዋትነት ይፈልጋል ስለዚህም አታጋዮቻችን መገንዘብ ያለባቸው የምንጠይቀው የሕዝብ መብት ወያኔ በችሮታ የሚሰጠን  የኛ ያልሆነ ሳይሆን ሰብአዊ ፍጡር በመሆናችን ልናገኝ የሚገባን እውነታችን እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ እናም ለእውነት ዋጋ ለመከፈል ዝግጁነት ያስፈልገናል፡፡ ትግሉ በከረረ ቁጥር ዘረኛው ስርዓት ማጣፊያ ሲያጥረው  ለሚወስደው ማንኛውም እርምጃ መቋቋም በሚያስችል መልኩ ጠንካራ አደረጃጀት ሊኖረን ግድ ይላል ፡፡

የወያኔ ዘረኛ ቡድን ህገ መንግስቱ የሚፈቅድልንን ለቁጥር የሚታክቱ መብቶቻችንን ቢነፍገንም፣ ሚያዚያ 30 1997ዓ.ም የነበረውን የቅንጅት የድጋፍ ሰልፍ ተከትሎ ለስምንት አመታት ቀምቶን የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ህገ መንግስታዊ መብታችንን ለማስመለስ ከአመታት በሗላ  በወጣቶች ለተደራጀው ሰማያዊ ፓርቲ  ምስጋና ይግባውና እጅግ በተጠና ወቅትና ጊዜ የመሰለፍ መብታችንን ከገዢዎቻችን እጅ አውጥቶ በሕዝቡም የተጫነውን የፍርሃት ድባብ በመግፈፍ እረገድ  ሃላፊነቱን ተወቷል፡፡
ከዚህ አኳያ የረፈደ ቢመስልም በአሁኑ ወቅት በሃገር ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴዎች ለዘረኛው ቡድን የራስምታት መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ስኬት ለሌሎቹ እንደ ማንቂያ ደውል በመሆኑ አንድነት ፓርቲም የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚል መሪ ቃል በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ እጅግ ፈታኝና ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ የተሳካለት ሊባል የሚችል ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል፡፡

99.6 የሕዝብ ድምጽ አለኝ የሚለው የወያኔ ዘረኛ ቡድን በመልካም አስተዳደር ችግርና በኑሮ  ውድነት እንዲሁም በፍትህ መጓደል የተንገሸገሸውን ሕዝብ በመፍራት ሰልፉን ለማደናቀፍ የቻለውን ያህል ቢጥርም መሰዋትነት ለመክፈል በቆረጡ የድርጅቱ አመራርና ጠንካራ አባላት ጥረት የታሰበውን ሰላማዊ ሰልፍ ማስተጓጎል ሳይቻለው ቀርቷል፡፡
ይህ የሚያሳየው በነፃነት የመኖር ሰዋዊ መብታችንን በአፋኝ አምባገነን መሪዎች መነጠቃችን ነው፡፡ ስለሆነም መብታችንን ለማስመለስ(ለማስጠበቅ) አስገዳጅ የትግል ስልት እንደሚያስፈልገን አጠያያቂ አይደለም፡፡ በመሆኑም አሁን ያለውን የሕዝብ ለነጻነትና ለትግል የመነሳሳት መንፈስ በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ ለማስቀጠል ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅብናል፡፡ በዘረኞች ለሚፈበረኩና ነጻነት የሚነፍጉ ህግጋቶችን እምቢ አሻፈረኝ የሚል ህዝብ ለመፍጠር የድርጅት አመራሮች ከዚህ በተሻለ በቁርጠኝነት መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
ድል ለኢትዮጲያ ሕዝብ!!!