Sunday, November 4, 2012

የመድረክ ሥራ አስፈጻሚን ጨምሮ በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱ ዘጠኝ ሰዎች ጥፋተኛ ተባሉ


ባለቤቴ ከሥራ እንድትወጣ በመደረጓ ልጆቼ ያለገቢ ለመኖር ተገደዋልየመድረክ ሥራ አስፈጻሚ
በታምሩ ጽጌ
ከሁለት ዓመታት በፊት ጥቅምት 1 ቀን 2002 .. በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት የመድረክ ሥራ አስፈጻሚና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋ መምህር አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች ስምንት ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ሕጋዊ ፓርቲን (ኦፌዴንና ኦሕኮን) ሽፋን በማድረግ ወጣቶችን በመመልመልና በማሠልጠን በተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦነግ) በህቡዕ እንዲሠሩ አድርገዋል በሚል ክስ ተመሥርቶባቸው ጥቅምት 22 ቀን 2005 .. የጥፋተኝነት ፍርድ የተላለፈባቸው አቶ በቀለ ገርባና አቶ ኦልባና ሌሊሳ ናቸው፡፡ 

ሌሎቹ የጥፋተኝነት ፍርድ የተላለፈባቸው ወልቤካ ለሚ፣ አደም ቡሳ፣ ሀዋ ዋቆ፣ መሐመድ መሉ፣ ደረጀ ከተማ፣ አዲሱ ሞክሬና ገልገሎ ጉፋ የተባሉ ግለሰቦች ሲሆኑ፣ የኦነግ አባል በመሆን በተለያዩ ቦታዎች ተማሪዎች እንዲረብሹ፣ ወጣቶችን በመመልመልና ኬንያ ድረስ ወስደው በማሠልጠን በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ መገኘታቸውንና ሌሎችንም ድርጊቶች ፈጽመዋል በሚል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸውን የሽብርተኝነት ወንጀል ማስተባበል አልቻሉም ተብሎ ነው፡፡ 

ሁሉም ተከሳሾች የተከሰሱበትን የሽብርተኝነት ወንጀል አለመፈጸማቸውን በመከራከር የመከላከያ ምስክሮችም አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን ክስና ማስረጃ ማስተባበል አለመቻላቸውን በመግለጽ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል፡፡ 

ጥቅምት 22 ቀን 2005 .. የጥፋተኝነት ፍርድ የተላለፈባቸው ዘጠኙም ተከሳሾች የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ተጠይቀው ማቅለያ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ባቀረቡት የቅጣት ማቅለያ እንደተናገሩትሕይወቴን በሙሉ አድልዎን፣ ኢፍትሐዊነትንና ዘረኝነትን በመቃወም በፈቃዴ ሳይሆን በፈጣሪ ፈቃድ፣ ለኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች መከበር በመታገሌና መስዋዕት በመሆኔ እኮራበታለሁ፤ብለዋል፡፡ በመቀጠልምይቅርታ መጠየቅ ካለብኝ የኦሮሞን ሕዝብ በደል በሚገባ ሳልገልጽ ቀርቼ ከሆነ፣ ወንድማማችነትንና አብሮ መኖርን አስቀድሜ ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ለግል ጥቅምና ለዝና ያደረኩትም ካለ እግዚአብሔርን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ሳላጠፋ የፈረደብኝን ፍርድ ቤት ቅጣቴን ያቃልልኛል ብዬ ይቅርታ መጠየቅ ባለመፈለጌ አዝናለሁ፤ካሉ በኋላ፣ ባለቤታቸው ከሥራ እንዲወጡ በመደረጋቸው ልጆቻቸው ያለገቢ ለመኖር መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡ 

ሌሎቹም ተከሳሾች የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውን፣ በሌላ ወንጀል ተጠይቀው እንደማያውቁ፣ ሕመምተኛ መሆናቸውንና ሌሎችንም ያቃልልናል ያሉዋቸውን ሐሳቦች ተናግረው የቅጣት ማቅለያ ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግም የቅጣት ማክበጃ ሐሳቡን ካቀረበ በኋላ፣ በጥፋተኞቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለኅዳር 14 ቀን 2005 .. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ አብቅቷል፡፡