Wednesday, July 17, 2013
በቦንድ ሽያጭ ያልተሳካው የገንዘብ ዘረፋ በኮንደሚኒየም ሰበብ መሳካት የለበትም!!!
ወያኔ በጠመንጃ ኃይል ሥልጣን ከተቆጣጠረበት 1983 ጀምሮ በከተሞች አካባቢ ምንም አይነት ሕዝባዊ ተቀባይነት ኖሮት አያውቅም። ለዚህም የሚሰጠው ምክንያት ከተሞች በጠላትነት በተፈረጀው አማራና የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች የተሞሉ ስለሆነ ነው ይላል። ዋና ከተማችን አዲስ አበባ በዚህ ውንጀላ ዋጋ ከከፈሉት ከተሞች ግንባር ቀደሟ ናት። በተለይ በመጀመሪያው የወያኔ 10 (አሥር) የሥልጣን አመታት የከተማዋን የነዋሪዎች አሰፋፈር ስብጥር ሆን ብሎ ለመቀየር ከመሞከር ጀምሮ የተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ተቋሞችን አቅም ለማዳከም በርካታ አሳዛኝ እርምጃዎች ተወስደዋል።
ታሪክን ወደኋላ መለስ ብለን እንቃኝ። የፋሺስት ጣልያን ጦር በእንግሊዝ ጦር ትብብር በኢትዮጵያ አርበኞች ከተደመሰሰ በኋላ በአሸናፊነው ወደከተሞች የገባው የእንግሊዝ ጦር ያገኘውን ንብረት በወቅቱ የቅኝ ግዛቶቹ ወደ ነበሩት ኬንያና ሱማሌ አሽሽቷል። ከብዙ ዓስርተ ዓመታት በኋላ ወያኔ ይህንኑ እኩይ ተግባር ደገመው። ወያኔ በያዛቸው ከተሞች ውስጥ ያገኘኛቸውን ውድ ዋጋና ትላልቅ ጥቅሞች የሚሰጡ በርካታ ንብረቶችን ከተለያዩ መንግሥታዊና ወታደራዊ ተቋሞች፤ ዩኒቨርስቲዎች፤ ሆስፒታሎች፤ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ አገልግሎት መስጫዎች ዘርፎ እስከዛሬ ትክክለኛ አደራሻው ለሕዝብ ይፋ ወደ አልተደረገ የሰሜን አካባቢ አይናችን እያየ በረጃጅም የጭነት መኪናዎች አጓጉዞአል። በቀድሞ መንግሥት ዘመን ምንም ዕጥረት እንዳልነበረው የሚታወቀውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የ24 ሰዓት መብራት አገልግሎትን እንኳ ሳይቀር በማስተጓጎል የከተማውን ሕዝብ ተበቅሎአል።
ወያኔ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ጥላቻ በጥቂቱም ቢሆን ረገብ ያደረገ የሚያስመስል እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የጀመረው በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው። አንደኛው ምክንያት በቃኝ የማያውቁት የቀድሞ ተጋዳላዮች የአገሪቱን አንጡራ ሃብት እንዲበዘብዙ በተመቻቸላቸው እድል ዘርፈው የያዙትን ገንዘብ ከውልደታቸው ጀምሮ ከሚታወቁበት አካባቢ ሕዝብ እይታ አርቀው “ለደም ካሳ” በዋና ከተማችን እምብርት በነፃ በታደላቸው የከተማ ቦታዎች ላይ ህንጻዎችን በመገንባት ንብረት እንዲይዙ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በርካታ የአለም አቀፍ ድርጅቶችና ዲፕሎማቶች መቀመጫ በሆነቺው አዲስ አበባ ምርጫ 97ን ተከትሎ ገጥሞት የነበረው ሽንፈት ባስከተለው መዘዝ የተበላሸ ገጽታውን በህንጻና መንገዶች ግንባታ ስም ለማሳመር መጣር ናቸው።
የአዲስ አበባ ኮንደሚኒዬም ቤቶቾ ግንባታ ከምርጫ 97 ቦኋላ በመኖሪያ ቤቶች እጥረት የሚሰቃየውን ሕዝብ ልብ ለማማለልና የፖለቲካ ድጋፍ ለመግዛት ያስችላል ተብሎ የታሰበ ብቻ ሳይሆን የሚከተሉት ድብቅ ዓላማዎችም አሉት።
- በዘረፋ የከበሩ የቀድሞ ተጋዳላዮችና የጥቅም ተካፋዮቻቸው አይናቸው ያረፈባቸውን ቁልፍ የመኖሪያና የንግድ ቦታዎች ሁሉ ለዘመናት በባለይዞታነት ይዘው የኖሩትን በልማትና በእንቨስትመንት ሥም በማፈናቀል ወደ ግላቸው ላማዞር ያስችላቸዋል፤
- በተለያዩ ሥም የተቋቋሙ የህንጻ ሥራ ተቋራጭ ድርጅቶቻቸው በግንባታው ሥራ በመሳተፍ መጠነ ሰፊ የሆነ ትርፍ ለማግበስበስ ያመቻቸዋል፤
- የሥርዓቱን ደጋፊዎችና አቀንቃኞች ከሌላ ቦታ አምጥቶ በማስፈር በጠላትነት የተፈረጀውን የኅብረተሰብ ክፍል ተጽዕኖ ለማምከን ይረዳል፤
- በሀብት ዘረፋው ለመሳተፍ እድል የሌላቸው የበታች ካድሬዎችና ታማኝ አገልጋዮችን ተጠቃሚ በማድረግ በአለቆቻቸው ዘረፋ ተማረው ልባቸው እንዳይሸፍት ይከላከላል ፤
- ከተወለዱበትና ካደጉበት የግልና የቀበሌ ቤቶች ያለውደታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች የኮኖዶሚኒየሙን ሂሳብ መክፈል እስከቻሉ ድረስ “ከቤታችን ተፈናቅለን ሜዳ ላይ ተጣልን” የሚል እሮሮ በማሰማት መንግስት ላይ አመጽ እንዳያስነሱ ስጋት ለመቀነስ ይረዳል፤
- ከሰሞኑ 40 ከመቶ ተብሎ በወጣው ፖሊሲ እንደታዘብነው ደግሞ ዜጎችን በማጓጓት ተቸግረው ያጠራቀሙትን ገንዘብ ዝግ የባንክ ሂሳብ ውስጥ እንዲከቱ በማድረግ የገንዘብ እጥረት አንገቱ ድረስ የዘለቀውን አገዛዝ ለመታደግ ያስችላል (በ16 የሥራ ቀናት ብቻ ከተመዘገበው 750, 000 የኮንዶሚንዬም ቤት አመልካች 750 000 000 (ሰባት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን) ብር መሰብሰቡን ልብ ይሏል)
ከዚህም በተጨማሪ የኮንደሚኒዬም ቤቶች ግንባታ በቂ ጥናትና ዝግጅት ያልተደረገበት የይድረስ ይድረስ ሥራ መሆኑን የቤቶቹ ርክክብ በተፈጸመ ማግሥት ስለ ህንጻው መሬት ውስጥ መስጠምና መጣመም መጀመር እየወጥ ያሉ ዜገባዎች ዋቤ ምስክር ናቸው።
የወያኔ መሪዎችና ታማኝ አገልጋዮቻቸው ከኮንደሚኒዬም ግንባታ በተጨማሪ ከምርጫ 97 ወዲህ ከፍተኛ ገንዘብ እያግበሰበሱ ያሉት የከተማ ቦታዎችን በውድ ዋጋ የልጅ ልጆቻቸው እንኳ ሊደርሱበት ለማይችል የግዜ ገደብ በሊዝ በመቸብቸብ ነው። በዚህ የመሬት ቅሪሚያ አንዳንድ ስግብግቦች “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” እንዲሉ “ወያኔዎች መሬታችንን እየተቀራመቱ ስለሆነ ተሻምተን ማስቆም አለብን” በሚል ብልጣ ብልጥነት ከሚኖሩበት የስደት አገር እየተጓዙ የወያኔን ገቢያ በማድራት ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በትዝብት ተመልክቶአል። አገርን ዘርፎ ለዘራፊ እየሰጠ ያለ መንግሥት ሴራ ተባባሪ መሆን በሞራልም ሆነ በህሊና ዳኝነት የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑ ሳያንስ እነዚህ በስግብግብነት የተጠመዱ ወገኖች ለንብረታቸው ደህንነት ሲባል ወያኔ ዓይናቸው እያየ ጆሮአቸው እየሰማ በሌሎች ወገኖቻቸው ላይ የሚፈጽማቸውን ሰቆቃዎች እንኳ ለመቃወም ድፍረት በማጣት ሌላ ትዝብት ውስጥ ሲወድቁ ተስተውለዋል:: ለመሆኑ እነዚህ ወገኖች ለፍተው ባገኙት ገንዘብ የገዙት ባርነትን ነው ወይስ የንብረት ባለቤትነትን ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይኖራቸዋል?
የዜጎች መብት በተከበረበት አገር ከዜግነት መብቶች አንዱ የግል ሀብት ባለቤት ለመሆን ገደብ የሌለው ነፃነትና እድል መኖሩ ነው:: ወያኔ በሚያስተዳድራት ኢትዮጵያችን ግን የንብረት ባለቤት ለመሆን የሥርዓቱ ባለሟል መሆን አለያም ከፖለቲካ ባላንጣነት መራቅ ዋና መስፈርት ናቸው። በዚህ መስፈርት ከወያኔ ጋር ተሻምተው ወይም ተሻርከው የንብረት ባለቤት ለመሆን እየተሽቀዳደሙ ያሉ ወገኖች ሊያውቁት የሚገባው ሃቅ ቢኖር አድሎአዊነት በሰፈነበት መንገድ የተገኘ ማንኛውም አይነት ሀብት ወይም ንብረት ወደፊት በወያኔ ከርሰ መቃብር ላይ በሚመሰረተው ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ህገዊ ጥበቃ የሚኖረው አለመሆኑን ነው። ብሄራው የአገር ጥቅም ላይ ክህደት ከፈጸመ ፤ ዜጎችን በማፈን ሰቆቃ ካደረሰ ፤ የአገሪቷን ዜጎች ከቤት ንብረታቸው በማፈናቀል መሬታቸውን ቀምቶ ለሌሎች አሳልፎ ከሰጠ ፤ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ዘርፎ ለዘራፍ ከሰጠ ወንጀለኛ መንግሥት ጉያ ውስጥ ተወሽቆ እስከ ወዲያኛው የህግ ጥበቃ ሊደረግለት የሚችል ንብረት ባለቤት መሆን ማሰብ እጅግ ይቸግራል። ዜጎች በራሳቸው ወዝ ለፍተው ያገኙትን ንብረት ሳይቀር በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ምክንያት ብቻ በሽብርተኝነት እየፈርጀ የሚነጥቅ ሥርዓት ዕድሜ እንደምንጠብቀው ረዥም ሊሆን እንደማይችል ማሰብ ብልህነት ነው።
ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የወያኔ አገዛዝ በውጭው ዓለም በስደት ከሚኖረው ወገናችን በአባይ ግድብ የቦንድ ሺያጭ ሥም ለመሰብሰብ ሞክሮ ያልተሳካለትን ገንዘብ በመሬት ሺያጭ እና በኮንደሚኒዬም ቤት ግዥ ሥም እንዲያገኝ ሊፈቀድለት አይገባም ብሎ ያምናል:: ስለዚህም እያንዳንዱ ነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ ከዚህ ከኮንደሚኒዬም ቤቶች በስተጀርባ ያለውን ድብቅ አጀንዳ በማጋለጥ ጥረቱን በማምከን የሕዝባዊ እምብተኝነት ትግል አካል እንዲሆን ግንቦት 7 የትግል ጥሪውን ያስተላልፋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ
Subscribe to:
Posts (Atom)