ህወሓትና ስዩም መስፍን በኢህአዴግ ምክር ቤት ድምጽ ተነፈጉ!
September 16, 2012 01:57 pm By Editor 7 Comments
የመከላከያውንና የደህንነቱን የስልጣን ርካብ ከቀድሞው ይልቅ ቆንጥጦ ለመያዝ እየተረባረበ ያለው ህወሓት በግልጽ ከሚታየው የፖለቲካ አመራር ወንበሩ ተነሳ። ለ21 ዓመታት የድርጅት፣ የጠ/ሚኒስትርነትና ቁልፍ የስልጣን መደቦችን ተቆጣጥሮ የኖረው ህወሓት ሁለቱን ግዙፍ ወንበሮች ለማስጠበቅ በድርጅትና በጎንዮሽ ትስስር ያካሄደው ዘመቻ አልተሳካለትም።
ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ አቶ መለስን የሚተካ መሪ መሰየም አለመቻሉን አቶ በረከት ስምኦን ያሳበቁበት ህወሓት በቀጣዩ ምርጫም ወንበሩን እንደማያገኘው አቶ በረከት በግልጽ ተናግረዋል። ኢህአዴግ ቀጣዩን ምርጫ ካሸነፈ ሁለቱ አዲስ ተሿሚዎች በስልጣናቸው እንደሚቀጥሉ በይፋ ተናግረዋል።
የኢህአዴግን የአመራር ወንበር ላለማጣት ያደረገው ሙከራ በየድርጅቶቹ በተካሄደ የተናጠል ስብሰባ ተሞክሮ ሊሳካ እንዳልቻለ ጎልጉል ምንጮቹን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል። በስም ተጠቅሰው ኢህአዴግን እንዲመሩ የቀረቡትን የህወሃት ሰዎች አንቀበልም ያሉት አባል ድርጅቶች በተቃራኒ በቀጣዩ የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ መተካካቱ በተዋጽዖ የተመጣጠነ እንዲሆን የሚያሳስብ ጥያቄ ማንሳታቸውን የጎልጉል ምንጮች ጠቁመዋል።ከአቻ ድርጅቶቹ በተጨማሪ አሜሪካ ያስተላለፈችው መመሪያም ተጽዕኖ መፍጠሩ ተገምቷል።
ለዚህ ይመስላል አቶ በረከትና አቶ ሬድዋን ሁሴን በሂልተን ሆቴል በሰጡት መግለጫ ላይ “አቶ ኃይለማርያም የራሳቸውን ካቢኔ የመመስረት ሙሉ መብት አላቸው” በማለት አቶ በረከት የቀድሞው ካቢኔ ሊፈርስ ወይም ማስተካከያ ሊደረግበት እንደሚችል አመላክተዋል።
የህወሓት/ኢህአዴግን አካሄድ በመገመትና በመተንተን የሚታወቁት ረዳት ፕሮፌሰር መድኔ ታደሰ ሴፕቴምበር 14 ለአሜሪካ ሬድዮ የአማርኛው ዝግጅት ክፍል በሰጡት ማብራሪያ አሁን ተፈጠረው አጋጣሚ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ለውጥ ማስከተሉ አይቀሬ መሆኑን አስረድተዋል። አያይዘውም መለስ በሌሉበት ሁኔታ የቁጥጥር አስተዳደር ማራመድ እንማይቻልም አመልክተዋል። ከቁጥጥር ይልቅ ወደ መመካከርና አብዛኞችን ወደሚያሳትፍ አመራር እንደሚለወጥ ተናግረዋል።
ተተኪ ሊቀመንበር ለመሰየም ሲሳብና ሲጎተት የከረመው ኢህአዴግ ራሱ ካወጀው የአቶ መለስ ህልፈት ከሃያ ስድስት ቀናት በኋላ አስቀድሞ በስፋት የተተነበየውን ሹመት ይፋ አድርጓል። በዚሁ መሰረት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝና የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ምክትል አድርጎ ሰይሟል። አቶ ኃይለማርያም “ምደባው የመስዋዕትነት ነው” ሲሉ ለመንበራቸው ያላቸውን ቁርጠኛነት ለጓዶቻቸው አረጋግጠዋል። ህወሓትን ወክለው አቶ ስዩም መስፍን ለምርጫ ቢወዳደሩም ድምጽ በማጣታቸው ሳይመረጡ ቀርተዋል።
ብቸኛው የመረጃ ምንጭ ኢቲቪ መስከረም 4 ቀን 2005 ዓ ም በምሽቱ ሶስት ሰዓት የዜና እወጃው ቀንጭቦ ባቀረበው ምስል አቶ ኃይለማርያምና ምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮንን በኢህአዴግ ምክር ቤት የአመራር ወንበራቸው ላይ ጎን ለጎን ተቀምጠው ታይተዋል። አቶ ኃይለማርያም ይህን ጊዜ ነበር “ምድባው ለመስዋዐትነት ነው፤ ምደባው ህዝብ ከኢህአዴግ የሚጠብቀውን በሙሉ ለመፈጸም ነው፤ ምደባው በሙሉ በኢህአዴግ ምክር ቤት አባላትና በናንተ ሙሉ ምክር ከኋላና ከፊት በምታደርጉት ጥረት የተደረገ ነው …” በማለት በተሳሰረ አንደበት የተናገሩት።
ሙሉ የኢህአዴግ ምክር ቤትን ያመሰገኑት አቶ ኃይለማርያምና አቶ ደመቀ ለደንብ ያህል ቃለ መሃላ መፈጸም ብቻ የሚቀራቸው ጠ/ ሚኒስትር ም/ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን አቶ በረከት ከጉባኤው መጠናቀቅ በሁዋላ በግልጽ ተናግረዋል። በዚሁ መሰረት በወስከረም ሶስተኛ ሳምንት አቶ ሃይለማርያምና አቶ ደመቀ የአዲሱን በትረ ሹመት ስርዓተ ፓርላማ ያከናውናሉ። የአቶ ሃይለማርያም ባለቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬም ቀዳማዊት እመቤት ሆነው አራት ኪሎ ከነቤተሰቦቻቸው ይዘልቃሉ።
ህወሓት አቶ ስዩምን አቅርቦ መሸነፉን ኢቲቪ አሳብቋል። 180 አባላት ያለው የኢህአዴግ ምክር ቤት ያካሄደውን ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ቅዳሜ ምሽት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያስተላለፈው ኢቲቪ ድምጽ ቆጠራውን ሲያሳይ የአቶ ስዩም መስፍን ስም በድንገት ታይቷል። የጎልጉል ዘጋቢ ከአዲስ አበባ እንዳረጋገጠው ኢቲቪ የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት ለውጪ አገር ዜጎችና ዲፕሎማቶች ለማሳየት ባሳየው ፊልም ላይ የታው የድምጽ መስጫ ወረቀት ሶስት ስሞች ያሉበት ነው። የአቶ ስዩም ስም በሶስተኛ ደረጃ ላይ ታይቷል። አቶ በረከት ስም አይጥቀሱ እንጂ ሶስት እጩዎች ለውድድር ቀርበው እንደነበር ማረጋገጣቸውን አገር የሰማውን ወሬ “ሰበር ዜና” ሲል ያጋጋለው ሪፖርተር አስታውቋል።
ለጊዜ ማግኛ የአቶ መለስ ህልፈት ምስጢር ተደርጎ በድርጅት ውስጥ ለውስጥ የነበረው ሽኩቻ ከረገበ በኋላ በጋራ የተያዘውን አቋም ሲያንከባልል የቆየው የኢህአዴግ ምክር ቤት ህብረተሰቡንና የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚማጸን መልዕክት አስተላልፏል።
“በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ለምትንቀሳቀሱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች” በማለት ኢህአዴግ በመግለጫው ያልተለመደ ውዳሴ አቅርቧል። “በጽሁፍና በአካል በመገኘት በሃዘናችን ስላጽናናችሁን እናመሰግናለን” ያለው መግለጫው በማያያዝ ስለ ምርጫና ስለ አብሮ መስራትም ጠቁሞ አልፏል።
“…አብረን እንሰራለን። በሚያለያዩን ጉዳዮች ላይ በሰለጠነ መንገድ ለመወያየት ዝግጅታችንን እንገልጻለን” ሲል ቃል የገባው ኢህአዴግ ተቋማዊ ለውጥ ስለመደረጉ የሰጠው ፍንጭ ግን የለም። አሁን በስራ ላይ ያለውን ምርጫ ቦርድ ይዞ ኢህአዴግ ስለ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ መናገር አይችልም። የመድረክ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ገብሩ አስራት ህወሓት/ኢህአዴግ በትግራይ ተቃዋሚዎችን ከነድራሹ ለማጥፋት እየሰራ መሆኑን በተለይም ህወሓት ይህንኑ በተደጋጋሚ በይፋ መግለጹን ባለፈው አርብ ለአሜሪካ ሬድዮ ተናግረዋል። በዚህ መነሻ የኢህአዴግ የእንተባበር ጥሪ የተለመደ ማደናገር እንደሆነ ተደርጎ ተወስዶበታል።
የፖለቲካውን ወንበር የተነጠቀው ህወሓት የጦር ሃይሉን፣ ፖሊስንና ደህንነቱን ቆንጥጦ መያዙ አገሪቱን ወደ ወታደራዊ አስተዳደር እንዳያመራት ስጋት የገባቸው ክፍሎች አቶ ኃይለማርያም የጦር ሃይሎች ዋና አዛዥነት ይስሙላ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ጎልጉል የአዲስ አበባ ምንጮቹን ጠቅሶ ከምርጫው ሶስት ቀን አስቀድሞ ህወሓት በፖለቲካው የአመራር ሰጪነቱ ሚና እንዳከተመበት በመረዳቱ የጦር ኃይሉና ደህንነቱ ላይ ያለውን አቅምና ኃይል ለማጠናከር ትኩረት መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል።ከተሿሚዎቹም መካከል የመጀመሪያዋን ሴት ጄኔራል (አስካለ ብርሃኔ ተድላ) ከአቶ መለስ ትውልድ ቦታ አድዋ ማድረጉ ለአብነት የሚጠቀስ ነው፡፡
በተመሳሳይ ዜና በስፋት ሲወራ ስለሰነበተው የሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሹመት ጉዳይ አቶ በረከት ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል። አቶ በረከት ቅዳሜ ምሽት በሒልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በቀጣይ ይሾማሉ ስለተባሉት ሶስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተጠየቁት ከጋዜጠኞች ነበር። ለጥያቄው መልስ የሰጡት አቶ በረከት “ሶስት ምክትል ጠ/ሚኒስትር የለም። የሚወራው ሁሉ ወሬ ነው። ኢህአዴግ ደግሞ በወሬ አይመራም” በማለት ትንበያውን አጣጥለውታል። አቶ በረከት ይህን ይበሉ ጉዳዩ እንደ አቶ መለስ ሞት ሰነባብቶ ይፋ ላለመሆኑ ማረጋገጫ የለም።
No comments:
Post a Comment