Tuesday, September 11, 2012

የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫ ንግግር September 11, 2012



    የተከበራችሁ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ እንኳን ከ2004 ዓ.ም. ወደ 2005 ዓ.ም. በሰላም አሸጋገረን። አዲሱ ዓመት በዘረኝነትና በአምባገነንነት ላይ ድል የምንቀዳጅበት ዓመት እንዲሆንልን በግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄና በራሴ ስም ከልብ እመኛለሁ።
    ይህን የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት ምክንያት በማድረግ በሶስት ጉዳዮች ላይ የድርጅቴንና የራሴን ምልከታዎች በአጭሩ እንዳቀርብ ይፈቀደልኝ።
    አንደኛ: ያለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ ፓለቲካ አንፃር ምን ዓይነት እንደነበር በማስታወስ በተለይም ለወደፊቱ ትግላችን አስተዋጽዖ ያላቸው አንኳር ጉዳዮችን አነሳለሁ
    ሁለተኛ ባለፈው ዓመት ድርጅታችን ካከናወናቸው ተግባራት ውስጥ በሕዝብ ቢታወቁ ከጉዳታቸው ጥቅማቸው ያመዝናል የምላቸውን አነሳለሁ
    ሶስተኛ በአዲሱ ዓመት፣ በ2005 ምን መሥራት ይጠበቅብናል በሚለው ርዕስ ንግሬን እቋጫለሁ።

    ክፍል አንድ: 2004 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ፓለቲካ

    ያሳለፍነው 2004 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ፓለቲካ ከፍተኛ እንደምታ ባላቸው ድርጊቶች የተሞላ ዓመት ነበር። በዓመቱ መጨረሻ ላይ የመጣው የመለስ ዜናዊ ሞት ሌሎቹን ታላላቅ ኩነቶችን እንዳይሸፈን አንዳንዶቹን እንዳስታውሳቸው ፍቀዱልኝ።
    1. በፀረ ሽብርተኝነት ህግ ሽፋን የተደረገው አፈና
    የመለስ አገዛዝ ዓመቱ የጀመረው ወያኔ ህጋዊ ብሎ በሚጠራው ማዕቀፍ ውስጥ የሚታገሉትን ዜጎች ከዚያ ማዕቀፍ ውጭ ከሚታገሉት ጋር በጭፍን አዳብሎ በሽብርተኝነት በመክሰስ ነው። በዚህም ምክንያት በርካታ ዜጎች ፈጽሞ ተገናኝተዋቸው ከማያውቋቸው ዜጎች ጋር በማበር ትሠራላችሁ ተብለው ተከሰዋል። በ2004 ዓ.ም. ሰላማዊ ብቻ ሳይሆን ፍጹም ሃይማኖታዊ ሰዎች እንኳን ሳይቀሩ በሽብርተኛነት እየተከሰሱ ወህኒ ወርደዋል።
    በ2004 ዓ.ም. አቶ ውብሸት ታዬ፣ ወ/ት ርዕዮት ዓለሙ፤ አቶ በቀለ ድሪባ፣ አቶ ኦልባና ሌሊሳ፣ አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ አቶ እስክንድር ነጋ እና በርካታ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን የዚህ አፋኝ ህግ ሰለባዎች ሆነዋል። በአቶ አንዱዓለም አራጌ መዝገብ ብቻ ሃያ አራት ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ የቆሙ የፓለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ እውነትን ለመዘገብ የደፈሩ ጋዜጠኞች፣ እና የማይታወቁ ሰዎች በበርካታ የፈጠራ የሽብር ወንጀሎች ተከሰው ሁሉም ጥፋተኞች ተብለው ከፊሎቹ በወያኔ እስር ቤቶች እየተሰቃዩ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ በሽብርተኝነት እየተከሰሱ በመታሰር ላይ ናቸው። በእስር ቤቶች የሚደረገው ሰቆቃ (ቶርቸር) በ2004 ዓ.ም. እጅግ ከፍቷል። የመለስ ዜናዊ የፀረ ሽብር ህግ ከኢትዮጵያዊያን አልፎ ለውጭ አገር ዜጎችም ተርፏል። የይስሙላ ችሎት በስዊድናዊያን ጋዜጠኞች ማርቲን ሽብየ እና ጆአን ፐርሰን ላይ የአስራ አንድ ዓመታት ጽኑ እስራት ቀጥቶ ዛሬ በእስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ።
    በዚሁ በሽብርተኝነት ክስ መዘዝ ጭል ጭል የነበረው ደካማው ነፃ ፕሬስ ጭራሹን ተዳፍኗል። የመጨረሻዎቹ የነፃው ፕሬስ ውጤቶች “አውራ አምባ ታምስ”፣ በቅርቡ ደግሞ “ፍትህ” እና “ፍኖተ ነፃነት” ታግደዋል። ከዚህ በተያያዘም ታዋቂ ጋዜጠኞችና አምደኞች ለስደት ተዳርገዋል።
    በአጭሩ 2004 ዓም የሰብዓዊ ጥሰቶች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱት ዓመት ነበር። እነዚህ እና ሌሎች በሺህዎች የሚቆጠሩ የዲሞክራሲ ታጋዮች የጣሉብን ኃላፊነት እጅግ ከፍተኛ ነው።
    2. መምህር የኔሰው ገብሬ
    በ2004 ዓም ትልቅ የታሪክ አሻራ አሳርፎ ያለፈ የዲሞክራሲ ሰማዕት መምህር የኔሰው ገብሬ ነው። ይህ የዳውሮው ወጣት መምህር፣ ኅዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም. በዋካ የአስተዳደር ቢሮ በረንዳ ላይ
    “በደል በዛ!!! ፍትህ በሌለበት አገር መኖር አልችም!!! በዚህ ሁኔታ መኖር ኑሮ አይባልም!!! ግፍና መከራ እያየሁ መኖር አልችልም!!!”
    እያለ ቤንዚን በራሱ ላይ አርከፍክፎ እሳት ለኮሰ። በቂ የህክምና እርዳታ ቀርቶ ጠያቂ እንኳን በወጉ አጠገቡ እንዳይደርስ በፓሊስ እንደተከለከለ በአራተኛ ቀኑ ሕይወቱ አለፈች።
    ኅዳር 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ኢትዮጵያም አንድ በፍትህ እጦት የተከፋና የተቆጣ ልጇን አጣች። ከመምህር የኔሰው ገብሬ በኋላም ቢያንስ ሌሎች ሁለት ኢትዮጵያዊያን ራሳቸው በእሳት አቃጥለው መሞታቸው ቢዘገብም ዜናቸው በስፋት እንዳይሰራጭ የአገዛዙ አፈና እንቅፋት ሆኗል።
    የመምህር የኔሰው ገብሬን አደራ እዳር ማድረስ ለ2005 የተላለፈ ሥራ ነው።
    3. ዝርፊያ
    2004 ወያኔ የሚያደርገው ዝርፊያ በከፍተኛ ሁኔታ የተጋለጠበት ዓመት ነው። የዓለም የፋይናንስ ኢቴግሪቲ (Global Financial Integrity) ባደረገው ጥናት መሠረት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2000 እስከ 2009 ባሉት 9 ዓመታት ውስጥ 11.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከኢትዮጵያ በህገወጥ መንገድ ወጥቶ መቅረቱ አረጋግጧል። 11.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማለት በአሁኑ ምንዛሬ 210 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ ነው። በዚሁ ሪፓርት መሠረት እ.አ.አ. በ2009 – በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ – የተዘረፈው መጠን 3.26 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማለትም 57 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ነው።
    ከዚህም በላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ማዕድን እና በጣም ሰፋፊ የሆኑ ለም መሬቶች የወያኔ አጫፋሪ ለሆኑ ግለሰቦች የተሰጡበት ዓመት ነው። በ2004 ወያኔ ኢትዮጵያን ዘርፎ፤ አዘርፏታል።
    4. መፈናቀሎችና እሮሮዎች
    ጉራ ፈርዳ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ ኦጋዴን፣ ወልቃይት 2004ን በዋይታና በእሮሮ ነው ያሳለፉት። በሺዎች የሚቆጠሩ ከአማራ ክልል የመጡ አርሶ አደሮች ከአስር ዓመታት በላይ ከሰፈሩበት መሬት ተነቅለው “ወደ አገራችሁ ሂዱ” ተብለው ለጎዳና ተዳዳሪነት ተጋርጠዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ ከሩቅ አገራት ለመጡ ሃብታም ኢንቨስተሮች መሬት ለመሸጥ በጋምቤላና በአፋር ድሆች ኢትዮጵያዊያን ከይዞታቸው ተፈናቅለዋል። ባለፉት ዓመታት እንደነበረው ሁሉ የመለስ አገዛዝ በኦጋዴን ላይ የሚያደርገው የጅምላ ጭፍጨፋ ቀጥሏል። የሲዳማ ተወላጆችም አካባቢያቸውን የማስተዳደር መብት በመጠየቃቸው ተዘምቶባቸው ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ ተደብድበዋል።
    እነዚህ ሁሉ ወረራዎች ኢትዮጵያዊያን በከፍተኛ ቁጥር እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያዊያን በአገር ውስጥም ስደት ውስጥ ናቸው፤ ከአገር ውጭም በከፍተኛ መጠን እየተሰደዱ ነው። 2004 የገጠር አርሶ አደሮች ወደ ደቡብ አፍሪቃ ሲሰደዱ የመያዛቸው፤ ባህር ውስጥ የመስጠማቸው፤ በኮንቴይነሮች ተከተው በመኪና ተጭነው ሲጓዙ ታፍነው የመሞታቸው መራር ዜናዎችን በብዛት የሰማንበት ዓመት ነው። 2004፣ ወደ አረብ አገራት የሚሰደዱ እህቶቻችን የሚደርስባቸው ዘግናኝ መከራዎችም በብዛት የተሰሙበት ዓመት ነው። ያም ሆኖ ግን የተሰዳጁ ቁጥር ከእለት እለት እየጨመረ ነው።
    5. ሕዝባዊ ተቃውሞዎች
    በ2004 የተደራጁና በተወሰኑ ክልሎች ያልተገደቡ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች የታዩበት ዓመት ነው። በዚህ አንፃር በ1997 ወዲህ 2004 ኢትዮጵያዊያን አብረው በጋራ የቆሙበት፤ ክልል ሳይገድባቸው ድምፃቸውን በጋራ ያሰሙበት ዓመት ነበር ማለት ይቻላል። በተለይም የሚከተሉት ሶስቱ ትኩረት የሚጠይቁ ናቸው።
    5.1. የመምህራን ተቃውሞ፤
    በ2004 ከታዩ የተደራጁ ተቃዉሞዎች አንዱ የመምህራን ተቃውሞ ነው። የአገዛዙ የውሸት ፋብሪካ በረከት ስምኦን “የኢትዮጵያ ገበሬ ከቢራ አልፎ ጉደር መጠጣት ጀምሮአል፣ መጠቅ ሲልም በአምባሳደር ሙሉ ልብሶች እንደ አደይ አበባ መፍካት ጀምሮአል” ቢልም የሕዝቡ ኑሮ ምን ያህል እየከበደ እንደመጣ ገላጭ ከሆኑት የሥራ መስኮች አንዱ መምህርነት ሆኗል። የኢትዮጵያ መምህራን የሚከፈላቸው ደመወዝ ለሳምንት እንኳን የማያደርሳቸው ቢሆንም እንኳን በረሃብ ምክንያት እያዞራቸው የሚወድቁ ሕፃናትን የመንከባከብ ኃላፊነትም ወድቆባቸዋል። የመምህራን የእለት ተእለት ኑሮ እያሽቆለቆለ ባለበት ሁኔታ እና ዓመታዊ የዋጋ ንረት ከ30 በመቶ በላይ በሆነበት አገር 7 በመቶ የማይሞላ ጭማሪ አድርጎ የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ በመሆናቸው የአዲስ አበባና የሌሎች ከተሞች ት/ቤቶች መምህራን የሥራ ማቆም አድማ መቱ። ይህ የሥራ ማቆም በአፈናና ድርጅት እጦት ምክንያት ብዙ ባይቆይም መልካም ትምህርቶችን ሰጥቷል። በተለይም የሙያ ማኅበራት በወያኔ መጠለፍ የሚያመጣውን ጉዳት በተጨባጭ ያሳየ ክስተት ነበር። በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ገናና ሚና የነበረውን የመምህራን ማኅበር፣ በወያኔ ተንኮል በመዳከሙ መምህራን በችግር ጊዜ የሚደርስላቸ ጠንካራ ማኅበር አላገኙም። ይባስ ብሎ ደግሞ ወያኔ ሰራሹ ተለጣፊ ማኅበር መምህራኑን ማሳጣቱ በግልጽ የታየበት አጋጣሚ ነው። ለጊዜውም ቢሆን የመምህራን እንቅስቃሴ ታፈነ። ይሁን እንጂ በዚህ የሥራ ማቋም አድማ መምህራን ለመብት የመታገልን አስፈላጊነት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተማሩ። የኢትዮጵያ መምህራን እያስተማሩ ያሉት በክፍል ውስጥ በሚሰጡ የቀለም ዘርፎች ብቻ ሳይሆን በተግባራዊ ህይወት ጭምርም መሆኑ በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው ተግባር ነው።
    5.2. የሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞ
    አሁን ዓመቱን ሊያከብር የተቃረበው የሙስሊም ኢትዮጵያዊያን የመብት ትግል የ2004 ዓ.ም. የፓለቲካ ድባብ የቀየረ ሲሆን የ2005 ንም የኢትዮጵያ ፓለቲካ በከፍተኛ ሁኔታ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ያነሷቸው ጥያቄዎች የመብት ጥያቄዎች ናቸው። “በሃይማኖታችን አትግቡብን ማለት” መብት ነው። “የማንፈልጋቸው የማኅበራችንን መሪዎች ሽረን የምንፈልጋቸውን እንምረጥ” ማለት መብት ነው። “በትምህርት ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ” ማለት መብት ነው።
    ግንቦት 7 የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የመብት ጥያቄዎች መደገፍ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ጥያቄዎች መሆናቸው ሲገልጽ ቆይቷል። የእምነት መብቶች የሰብዓዊ መብቶች አካል በመሆናቸው እና ሰብዓዊ መብቶች ደግሞ ሳይሸራረፉ መከበር እንዳለባቸው በጽኑ እናምናለን። ስለሆነም ሃይማኖት ሳንለይ አብረን ልንቆም ይገባል። ይህንን አቋማችንን በግልጽ ገልፀናል።
    በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ እስካለ ድረስ የእምነትም ሆነ ሌሎች ሰብዓዊ መብቶች ይከበራሉ ብለን ስለማናምን ትግሉ ወያኔን ወደማስወገድ እንዲያድግ ፍላጎታችን መሆኑም መግለጽ እንፈልጋለን።
    እስካሁን በታየው ብቻ እንኳን የሙስሊሞች ንቅናቄ በርካታ ጠቃሚ ልምዶችን ሰጥቶናል። ለምሳሌ፣ የድርጅትና የርዕዮተ ዓለም አስፈላጊነት በጉልህ አሳይቶናል።
    ክርስቲያን እና ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ለማከፋፈል በወያኔ ከፍተኛ ዘመቻ እየተደረገ ቢሆንም በተቃራኒው የሁለቱ ትላልቅ እምነቶች ተከታዮች የተቀራረቡበት ሁኔታ መፈጠሩ ተስፋ ሰጪ ነው።
    5.3. የክርስቲያኖች ተቃውሞ በዋልድባ
    የመለስ አገዛዝ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ቀኖና እንዲጣስና፤ ቤተክርስቲያኗ እንድትከፋፈል አድርጓል። በ2004 ዓ.ም. ደግሞ የእስካሁኑ አልበቃ ብሎት የዋልድባ ገዳም እና የቅዱሳን መካነ መቃብርን ደፍሯል።
    ዋልድባን ለመታደግ በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ብዙ ትግል ተደርጓል። በዚህ ትግ ውስጥ ሙስሊሞች በክርስቲያኖች ጎን መቆማቸው ትልቅ ተስፋ ሰጪ ነገር ነው።
    አሁን ደግሞ የፓትሪያኩ ሞት ተከትሎ በዋልድባ ላይ ተጨማሪ ጉዳይ መጥቷል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ጉዳይም ውሳኔ የሚሻ አቢይ ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጉዳይ የኢትዮጵያን ፓለቲካ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀይር ይሆናል ተብሎ ይገመታል።
    በበኩላችን ወያኔ እስካለ ድረስ የቤተክህነት ደንቦች ይከበራሉ ብለን ስለማናምን ትግሉ ወያኔን ወደማስወገድ እንዲያድግ ፍላጎታችን መሆኑም ለክርስቲያን ወገኖቻችንም መግለጽ እንፈልጋለን።
    ከእነዚህ ሌላ ጎልተው ባይወጡም ሌሎች እንቅስቃሴዎች ነበሩ። በአረብ አገራት የሚገኙ ዜጎቻችን በተለይም እህቶቻችን ምሬቶቻቸውን በገሃድ መግለጽ ጀምረዋል። በድርጅት ከታገዙ በ2005 ዓ.ም. መካከለኛው ምሥራቅ የዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አካል ማድረግ ይቻላል።
    6. የመለስ ዜናዊ ሞት
    በዓመቱ መጨረሻ ላይ የደረሰው የመለስ ዜናዊ ሞት በኢትዮጵያ ፓለቲካ ላይ ለውጥ የሚያመጣ አቢይ ክስተት ነው። የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ሁለት ክፉ ባህሪያትን አደባልቆ የያዘ ነበር። አንደኛው ፍጹም የሆነ የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ዘረኛነቱ ነበር።
    ፈላጭ ቆራጭአገዛዞች በጊዜ ተተኪ ካላዘጋጁ በስተቀር ከገዢው ሞት በኋላ ትርምስ ውስጥ ይገባሉ። እኛ ባለን መረጃ መሠረት መለስ ዜናዊ እንደሚሞት አስቀድሞ ያውቅ ነበር። ሆኖም ለሥልጣን ባለው ስግብግነቱ ሳቢያ እንደሚሞት እያወቀ ተተኪ አላዘጋጀም።
    እኛ “መለስ ለወያኔ ሁሉም ነገሩ ነው” ስንል ቆይተናል። እንዲያውም “ወያኔ” በማለት ፋንታ “የመለስ ዜናዊ አገዛዝ” እያልን ነበር አገዛዙን የምንገልፀው። አሁን ግን እኛ ካልነው እጅግ በላይ ራሳቸው በቴሌቪዥን እያሉት ነው። እራሳቸው እንደሚነግሩን ያለሱ የሚያስብ አንድም ጭንቅላት ወያኔ ውስጥ የለም። አንዱ ነባር ወያኔ “መለስ ህወሓትን ገድሎ ነው የሞተው” ብሏል የሚባለው እውነትነት አለው። ሃዘናቸው የበረታበትም አንዱ ምክንያትም ይህ ነው። ለመለስ ተተኪ ማግኘት ለወያኔ ከባድ ራስ ምታት ነው።
    ለመለስ ዜናዊ ተተኪ ከህወሓት ውጭ ለመፈለግ የወያኔ የአገዛዙ ሁለተኛ ባህርይ ማለቱም ዘረኝነቱ አይፈቅድለትም። የመለስ ዜናዊን ዘረኛና አምባገነን ሥርዓት ለማስቀጠል ሁለቱም ባህሪያት እንቅፋት ሆነዋል። በወያኔ ሹሞች ዓይን የኢህአዴግ አባላት የሚሏቸው ድርጅቶች ሹማምንት ባይሆን ለመነዳት እንጂ ለመምራት አይበቁም። ከፊት ሌላ ሰው ለማስቀደም ቢስማሙ እንኳን “ከኋላ ማን ሆኖ ይነዳል?” የሚለው ቀላል ምላሽ ያለው አይደለም።
    የሚገርመው የኦርቶዶክስ ቤተክነትም ውስጥ ተመሳሳይ ችግር መኖሩ ነው። እዚያም ዘረኝነትና አምባገነንነት ቤተክርስቲያኒቷ ሕጋዊ መሪ እንዳይኖራት እንቅፋት ሆነዋል።
    እነዚህ ሁኔታዎች የሚቀጥለውን ዓመት የኢትዮጵያ ፓለቲካ በከፍተኛ ሁኔታ ይወስናሉ ብለን እናምናለን። ከበረታን ለሁለቱም ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ በ2005 ማግኘት እንችላለን።

    ክፍል ሁለት፤ ግንቦት 7: በ2004 ዓ.ም.

    ለሚጠብቀን ትግል በቂ ነው ብለን ባናምንም በአለፈው 2004 ዓም፣ ግንቦት 7 በርካታ ሥራዎችን የሠራበት ዓመት ነው። ንቅናቄዎችን በአለፈው ዓመት ካደረጋቸው ተግባሮች ከፊሎቹን ከዚህ በታች ልዘርዝር
    1. ድርጅታዊ አቅም ግንባታ
    በአለፈው ዓመት ንቅናቄዓችን ያደረገው ትልቁ ነገር ድርጅታዊ አቅምን ማጎልበት ነበር። ይህ ውስጣዊ የመዋቅር ለውጥ ከማድረግ ጀምሮ የድርጅቱ አካላት በሙሉ በአንድ ዋነኛ ሥራ ላይ እንዲያተኩሩ የተደረገበትን ዓመት ነው። አሁን ድርጅታችን ወያኔን በማስገደድ ወይም በማስወገድ ሥራ ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል። በዚህም መሠረት ወያኔን ለማስገደድ ወይም ለማስወገድ የሚረዱ ወሳኝ ሥራዎችን እየሠራን ነው።
    2. አገራዊ ኅብረት መፍጠር
    በግንቦት 7 እምነት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጣው ለውጥ ሰላምን፣ እኩልነትን፣ መቻቻልን እና ፍትሃዊ ክፍፍል ያለበት ልማትን ማምጣት መቻል አለበት። በዚህም ምክንያት ከተለያዩ የፓለቲካ ድርጅቶችና ስብስቦች ጋር እርቅ መፍጠርና መደራጀት የሚገባን ከአሁኑ ጀምሮ መሆን ይኖርበታል ብሎ ያምናል። በ2004 ዓም በዚህ ረገድ ጥሩ ውጤቶች ተገኝተዋል
    2.1. ንቅንናቄዓችን ከኢትዮጵያ አንድነትና ፍትህ ንቅናቄ ጋር ውህደት ፈጥሯል። ሁለቱም ንቅናቄዎች ወደ ውህደት ከማምራታቸው በፊት የጥምረት ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለፍትህ በኢትዮጵያ (ጥምረት) አባል በመሆን ዓላማዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ድርጅታዊ ባህሎቻቸውም እንዲቀራረቡ አድርገዋል።
    2.2. በጄኔራል ከማል ገልቹ ከሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጋር በጣም ጥሩ የሆነ የሥራ ግኑኝነት ተፈጥሯል። እንደሚታወቀው በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጥላ ሥር ከሌሎች የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር ተባብሮ ለመታገል መወሰኑን ገሃድ አድርጓል። በዚህ ውሳኔ ሳቢያም በኢትዮጵያ የሰፈነውን ዘረኛ አምባገነን ሥርዓት አስወግደን በምትኩ የግልና የወል መብቶች የተከበሩባት፤ ፍትህና እኩልነት የሰፈኑባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በምናደርገው ትግል ውስጥ ኦነግ አዎንታዊ የሆነ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው የሚያደርግ አዲስ ሁኔታ ተፈጥሯል።
    በ2004 ዓም ጥምረትና ኦነግ በአምስት አገሮች ውስጥ በሚገኙ 11 ከተሞች ሕዝባዊ ስብሰባዎችን አካሂደው መደጋገፍ መጀመራቸውን በይፋ አሳይተዋል።
    2.3. ግንቦት 7 ከተለያዩ የፓለቲካና የሲቪል ማኅበራት ጋር ተቀራርቦ እየሠራ ነው።
    2.4. ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ለመተባበር የሚደረገው ጥረትም በቅርቡ ፍሬ ያፈራል ተብሎ ይጠበቃል።
    3. የሚዲያ አፈናን ለመቋቋም የተደረገ ጥረት
    ወያኔ ኢትዮጵያ ፈጽሞ የተዘጋች አገር ለማድረግ እየሠራ ነው። የኢንተርኔት ቁጥጥሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በስካይፕ ማውራት 15 ዓመት የሚያስቀጣባት አገር ሆናለች። የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን የመገናኛ ተቋም ከማለት የስለላ ተቋም ማለት ይሻላል። ራሳቸው በራሳቸው ሳንሱር እያደረጉ ተሸማቀው ይሠሩ የነበሩ፤ ተጠንቅቀውም ቢሆን እውነት ይናገሩ የነበሩ “ፍትህ” እና “ፍኖተ ነፃነት” ጋዜጦች ተዘግተዋል።
    ግንቦት 7 ለኢትዮጵያዊያን ነፃ መረጃ ማድረስ ግዴታችን ነው ብሎ በማመን ባደረጋቸው ጥረቶች ውጤቶችን ያስመዘገበ ድርጅት ነው። ወያኔ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን፣ በርካታ ራድዮኖችና ጋዜጦችን ይዞ ይፈራል። ለምሳሌ በሳምንት ለአንድ ሰዓት በኤርትራ ቴሌቪዥን የሚቀርበውን ቴሌቪዥንን ለማፈን ያደረገው የውንብድና ሥራ ከአረብ ሳት እንዲወርድ አድርጎታል። ንቅናቄዓችን የወያኔን የሚዲያ አፈና ለመሰባበር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ጥረት ማድረጉን ይቀጥልበታል። ይህ ሥራ ግን የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የጋራ ኃላፊነት መሆኑ ግንዛቤ አግንቷል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በሁላችንም የጋራ ጥረት አፈናውን እንሰብራለን።

    ክፍል ሶስት: በ2005 ምን መሥራት ይጠበቅብናል?

    አዲሱ 2005 ዓ.ም. በዘረኝነትና በአምባገነንነት ላይ ድል የምንቀዳጅበት ዓመት እንዲሆንልን ማድረግ የሚገባንን ነገር በአንድ ሃረግ ማስቀመጥ ይቻላል። ይህች ሃረግ – ወያኔን ማስገደድ ወይም ማስወገድ _ የምትል ናት።
    በ2005 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት ወያኔን በማስገደድ ወይም ማስወገድ ላይ መሆን ይኖርበታል። ኢትዮጵያዊያን ጊዜዓቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ሃብታቸውን ወያኔን ለማስገደድ ወይም ለማስወገድ በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ ብቻ እንዲያውሉ እንጠይቃለን።
    “ወያኔን ማስገደድ ወይም ማስወገድ” የምትለዋን ሃረግ በተለያዩ አቅጣጫዎች መተንተን ዓላማችንን ብቻ ሳይሆን ስትራቴጂያችንና ስልቶቻችንን ለማብራራት ይጠቅማል።
    1. ወያኔን ማስገደድ ለምን?
    ከአሁን በኋላ በአገራችን የመንግሥት ሥልጣን ምንጭ ሰላማዊ፣ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ የሆነ የሕዝብ ምርጫ ብቻ መሆን ይገባዋል። ወያኔን የመጨረሻው አምባገነን ማድረግ ይገባናል። አሁን ከምንገኝበት ዘረኛና አምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ምንመኘው የሕዝብ አስተዳደር በሰላማዊ መንገድ መሸጋገር የመጀመሪያ ምርጫችን ነው። ሆኖም ግን ከልምድ እንዳየው ወያኔ ለዚህ ዝግጁ አይደለም። ስለሆነም ወደዚህ ምርጫ እንዲመጣ ማስገደድ ይኖርብናል።
    2. እንዴት ይገደድ ?
    ወያኔን ለማስገደድ “እንቢ፤ አልገዛም” ማለት ይገባል።
    “እኔ ምን አቅም አለኝ” የሚለውን ቅስም ሰባሪ ሃሳብ ከአዕምሮዓችን ማውጣት አለበን። በአለፈው ዓመት ጋዜጠኛ አቶ አበበ ገላው አንድ ሰው ድምጹን ተጠቅሞ ምን ማድረግ እንደሚችል በተግባር አሳይቶናል። ግንቦት 10፣ 2004 ዓ.ም. አቶ አበበ
    መለስ ዜናዊ አምባነን ነው!!! ነፃነት እንሻለን!!! ነፃነት እንፈልጋለን!!! መለስ አምባገነን ነው!!! ነፃነት እንፈልጋለን!!! ነፃነት!!! ነፃነት!!! ነፃነት!!! ነፃነት!!!
    ብሎ መጮሁ በመለስና በወያኔ ወገን እስካሁን ያልሻረ ድንጋጤ፤ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ደግሞ ከፍተኛ መነቃቃትን መፍጠሩ የምናውቀው ነው።
    ከተደራጀን ደግሞ ከዚህ እጅግ በላይ የሆኑ ነገሮችን እንሠራለን።
    • ሙስሊም ወገኖቻች በሃይማኖት ነፃነት ጉዳይ እያደረጉት ያለው ትግል በዚያች አገር ውስጥ ወያኔ በራሱ ህገመንግሥት እውቅና የሰጣቸው የግለሰብና የቡድን መብቶች ያለምንም መሸራረፍ እስካልተከበረ ድረስ ምላሽ ያገኛሉ ብለን አናምንም። ስለዚህም መላው ኢትዮጵያዊ ጥያቄዎቹን ደግፎ በመነሳት ሙስሊምም ወገኖቻችን ያነሷቸው ጥያቄዎች ፍትሃዊ ምላሽ እንዲያገኙ አገዛዙን ማስገደድ እንዲችል ጥሪ እናደርጋለን።
    • ክርስቲያን ወገኖቻችን በፓትሪያርክ ምርጫ እና በዋልድባ ጉዳይ እያደረጉት ያለው ትግልም ከላይ ከገለጽኩት ተለይቶ የሚታይ አይደለም። በወያኔ የተሾሙትና በቤተ ክህነት ውስጥ የአገዛዙን መዋቅር በመዘርጋት ሕዝበ ክርስቲያኑን ሲከፋፍሉ የቆዩት ፓትርያርክ ህልፈት የፈጠረው አጋጣሚ በመጠቀም የቤተክርስቲያንቷ አንድነትና የምዕመናኑን ጥቅም የሚከበርበት አዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መታገል ይኖርበታል።
    • ከኦጋዴን፣ ከጋምቤላ፣ ከሲዳማ፣ ከወልቃይት፣ ከአፋር …ወዘተ ወገኖቻችን ጎን ቆመን ፍትሃዊ ጥያቄዎቻቸውን መደገፍ ይገባናል።
    • ከመለስ ጋር አብሮ መቀበር የሚገባው የወያኔ ዘረኛና ግፈኛ ሥርዓት ሌሎች መለሶችን እየፈለፈለ የመከራ እድሜያችን እንዳያራዝመው የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። የመለስ ዜናዊ ሞት የዘረኞችና የአምባገነኖች መንደርን የቀትር ጨለማ አልብሶታል። የሕዝብ ወገኖች ይህን አጋጣሚ በሚገባ ከተጠቀምንበት ዘረኞቹ ካሰፈኑብን የባርነት ጨለማ ወደ ነጻነት ብርሃን መቀየር እንችላለን።
    እድሎ ች ሲፈጠሩ መጠቀም ብቻ ሳይሆን እድሎቹንም መፍጠር ይኖርብናል። ወያኔ መግዛት የማይችልበት ሁኔታ ላይ ሲደርስ ለመደረደር ይገደዳል።
    3. ማስወገድ ለምን?
    አብዛኛውን ጊዜ አምባገነኖች ለሕዝብ ፍላጎቶች ተገዢ አይሆኑም። ለዚህም ነው በቅርቡ እንኳን የቱኒዚያ ቤን ዓሊ፣ የግብጹ ሙባረክ፣ የሊቢያው ጋዳፊ የተወገዱት። ሶሪያም ያለው ሁኔታ እያየነው ነው። ወያኔ ለሕዝባዊ ማስገደድ ደንታ ባይሰጥ ምላሻችን ማስወገድ መሆን ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል። ግንቦት 7 ይህንን ተግባር መሸሽ አንችልም ብሎ ያምናል።
    4. ማን ነው የማስገደዱን ወይም የማስወገዱን ሥራ የሚሠራው?
    ይህንን ሥራ የሚሠራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ሕዝብ ነው የትግሉም የድሉም ሙሉ ባለቤት።
    ወያኔን የማስገደድ ወይም የማስወገድ ሥራ ለጥቂት “ጀግኞች” የሚተው ሥራ አይደለም። ይህ ሥራ ለአርሶ አደሩ፣ ለላብአደሩ፣ ለመምህሩ፣ የዕለት ተዕለት የኑሮ መከራና የወያኔ የግፍ ቀንበር ጀርባውን ላጎበጠው የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ የሚተው አይደለም። በዚህ ወሳኝ ተግባር ላይ የሃገሪቱ ምሁራን ተሳትፎ አጽንዖት ሊሰጠው ይገባል። የገዛ ራሱ ክብር የሚሰጥ፤ የወገኑና የሃገሩ ውርደት የሚያንገበግበው የሃገሪቱ ምሁር ሁሉ በዚህ ትግል ውስጥ ተጨባጭ አስተዎጽኦ ማድረግ ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ምሁራን፣ የዘመናት መከራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ይህንን ትግል በሁሉም መስኩ ዘመናዊ በሆነ መንገድ የማደራጀት እና በእውቀትና በብቃት የመምራት ኃላፊነት አለባቸው።
    የገባንበት ትግል ከባድ፣ ውስብስብና መስዋዕትነትንም የሚጠይቅ ነው። ግንቦት 7 ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ይህንን ትግል ለመምራትና ግንባር ቀደም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጥላችኋለሁ።
    ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ወያኔን የማስገደድና የማስወገድ ሥራዎች ተደጋጋፊዎች ብቻ ሳይሆን አሁን ባለንበት ሁኔታ አንዱ ያለሌላው ዋጋ የለውም። “ነፃነትን እሻለሁ፤ በባርነት አልገዛም” የሚል ሕዝብ ከሌለ ነፃ የሚያወጣ ሠራዊት ቢኖርም አይጠቅምም። ወያኔ የሚፈራው ነገር ከሌለ ደግሞ “እንቢ ብሎ የተነሳን ሕዝብ” ከመፍጀት የማይመለስ እኩይ እንደሆነ እናውቃለን። ስለሆነም ሁለቱ መደጋገፍ ይኖርባቸዋል። ለዚህም ነው የትግል ስልታችንን “ሁለገብ” ያልነው።
    ሁለገብ የትግል ስልታችን እያንዳንዱ በሚስማማውና በሚያምንበት የትግል ስልት ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ እድል ይከፍትለታል። ሁለገብ ትግል በፍጥነትና በአነስተኛ መስዋዕትነት ወደምንፈልገው ግብ ያደርሰናል ብለን እናምናለን።
    ከእንግዲህ በአገራችን የመንግሥት ሥልጣን ሰላማዊ፣ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ ከሆነ የሕዝብ ምርጫ ብቻ መፍለቅ ይኖርበታል እንላለን። ይህ እንዲሳካ ደግሞ በቅድሚያ ወያኔን ማስገደድ ወይም ማስወገድ ግዴታችን ነው።
    ግንቦት 7 የሚጓዝበትን መንገድ በጥቃቄ የተለመ፤ ወያኔን ለማስገደድ ወይም ለማስወገድ ምን መደረግ እንዳለበት፤ ቀጥሎ የሚመጣው የሽግግር መንግሥት ምን ቅርጽና ይዘት ሊኖረው እንደሚገባ፤ ሰላማዊ፣ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ ከሆነ የሕዝብ ምርጫ ለማካሄድ ምን ዓይነት ተቋማት ሊገነቡ እንደሚገባ ዝርዝር ስትራቴጂያዊ እቅድ አውጥቶ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው።
    አስቀድሜ እንዳልኩት ግንቦት 7 ግንባር ቀደም መስዋዕትነት ለመክፈል እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር ትግሉን ለመምራትና ዝግጁ ነው። ተከተሉን፣ ደግፉን።
    2005 ዓ. ም. ከወያኔ ዘረኝና አምባገነናዊ አገዛዝ የምንገላገልበት የድል ዓመት ያድርግን።
    መልካም አዲስ ዓመት

No comments: